የመጅሊስ ምርጫ፡ ከ’ግሎባል’ ወደ ‘ማዘጋጃ’
ግንቦት 2/2004
በ2001 የቀድሞ መጅሊስ ሹማምንት የእነ አቶ ኤሊያስ ሬድማን ቡድን እንዝህላልነትን ለማረምና ሙሰኞችን ለፍርድ ለማቅረብ በሚል ሰበብ በግሎባል ሆቴል በተሰየሙ ጉባዔተኞች አዲስ፤ ታማኝና የአህባሽ ጥምቆች (ቅምጦችም ይሆናሉ- የፖለቲካ)፤ አረንጓዴ ጠምጣሚዎች አቶ አህመዲን ጨሎን ራስ አድርገው ሌሎች ደግሞ በተዋረድ ተሹመው (ተመርጠው አላልኩም) በጓሮ በር ወንበሩን ያዙት፡፡ እኛም ከዛሬ ነገ አቶ ኤሊያስ በ50 ሚሊዮን ብር ሙስና ተከሶ ፍርድ ቤት ሲቆም (ወይም ሲቀመጥ) ለማየት በጉጉት ስንጠብቅ፡ ስንጠብቅ …. (የዋሆች!) ተረስቶ ቀረ- ወይ አለማወቅ! ለካስ ለመሾም ሙስና ዋነኛ መስፈርት ሆኖ ኖሯል!
እነ ጨሎም ቢሮውንና ሙስናውን ከተላመዱ በኋላ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ’አህባሽ’ን የማጥመቅ ዘመቻ እንደ ዋና የቤት (ቢሮ) ስራ ተሰጥቷቸው ተረከቡ፤ ከዚያም ቅድመ-ማፅዳት ስራ ጀመሩ፡፡ ‘IIRO’ን ማባረር፣ አወሊያን መረከብ፣ ለመንግስት መረጃ ማቀበል፤ የሙስሊሙን የልብ ትርታ መለካት ወዘተ…. (ስንቱ ይዘረዘራል??)..
በመጨረሻም ከሊባኖስ 200 የአህባሽ “ዓሊሞችን” በማስመጣት በሃምሌ 2003 በሐረር ከተማ ማጥመቁን በይፋ ጀመሩት፡፡ ቀጥሎ በሌሎችም ቦታዎች አፋፋሙት፡፡ ህዝበ-ሙስሊሙም ነገሩን በሹክሹታ፤ በፊት-መፅሃፍ
(facebook) ጫካ፤ በጋዜጣና መፅሄቶች መቃወሙን ተያያዘው፡፡ ተቃውሞው በውጭ ሃገራት አይሎ ነበርና በNovember 21, 2011 በአሜሪካ የተቃውሞው ሰልፍ ፈነዳ፡፡ በሀገር ውስጥ ግን ፍርሃት እንደነገሰ ነው፡፡ ሆኖም በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ የአወሊያ ኮሌጅ መዘጋትና መምህራንና ኢማም መባረርን ተከትሎ በጀግኖች የአወሊያ ተማሪዎች አገር ውስጥም የተቃውሞ ሰልፍ ፈነዳ፡ አዲሳባዎችም አጎራባቾችም ሆኑ ክፍለ-ሀገሮች ከቤታችው፤ የፊት-መጽሀፍ
(facebook) ታጋዮችም ከጫካው በመውጣት የተቃውሞ ትግሉን ተቀላቀሉ፡ የቅሬታ ፊርማም ተጧጧፈ፤ ጥያቄውም ከአወሊያ ጉዳይ ወደ መጅሊስ ይውረድ አደገ፤ መጅሊሶችም ጨነቃቸው፤ ተቃውሞውም ጠነከረ፤ በኮሚቴ ተዋቀረ፤ ወደ ክፍለ-ሀገርም ተሰራጨ፡፡ ሀገራዊም ሆነ፡፡
ተቃውሞው እስካሁን የተዋጣለት አካሄድ መሄድ ችሏል፤ ከመቼውም በላይ አንድነት ጠንክሯል፤ ድጋሜ ላይላላም ሙስሊሞች ተማምለዋል፤ ግፊቱ አንዋር መስጅድ ላይ ከትሟል፤ የመንግስት ባለስልጣናትንም አወዛግቧል፤ ወደ ዓለምም ተስተጋብቷል፡፡
በጀት ለ2004
መጅሊስም በጥር ወር ላይ የ2004 አመታዊ በጀቱን ይፋ አደረገ፤ 636 ሚሊዮን ብር!! (“ከየት መጣ?” ብሎ መጠየቅ ያስቀስፋል!) “ለአወሊያም 6 ሚሊዮን ብር ስለተመደበለት ሰልፉን ትታችሁ ወደ ቤታችሁ ግቡ” ተባለ!! “አል-ቁድስ” ጋዜጣም ተገዛ፤ በቅርቡም የሀገር ውስጥ ዊኪሊክስ ይፋ እንዳደረገው ከበጀቱ ውስጥ 203 ሚሊዮን ብር የሚሆነው በአቶ ጨሎ ልጅ የግል ቁጠባ ሂሳብ መግባቱን፤ ለ”አል-ቁድስ” ጋዜጣ በየወሩ 88ሺህ ብር መሰጠቱን፤ አብዛኛው ገንዘብ ለአህባሽ ስልጠናና ለጫት ወጭ እንደሚውል መታቀዱን ሰማን- ጆሮን አትስማ አይሉት፡፡
የጉልቻ ለውጥ ዜና
አሁንም በሀገር ውስጥ ዊኪሊክሰ መረጃዎች መሰረት ሚያዚያ 19/2004 እጅግ መራር ዱብ እዳ ወረደ! በአቶ መለስ የፀጥታ አማካሪ፤ የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋዬ በርኸ እና በፌዴራል ጉዳዮች ሚ/ር ‘ሙፍቲ’ ሽፈራው ተ/ማሪያም በኩል መጅሊሶች ከስልጣናቸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲወርዱ ተነገራቸው፤ መቼም “ከስልጣንና ከጫት ላይ መነሳት ይከብዳል" ይላሉ- የሚያውቁት፡፡ እናም የኦሮሚያና የአዲሳባ መጂሊሶች አለቃቀሱ አሉ፤ ምርጫም በሰኔ ወር እንደሚካሄድ ተነገራቸው (ለነገሩ ከአሁን በኋላ ምን ሊያደርግላቸው- እኛ ከወረድን ሰርዶ አይብቀል ነውና ነገሩ!)- በፌዴራል ጉዳዮች ሚ/ር በጀት መዳቢነትና አመራር ሰጪነት ብሎም በዑለማዎች ም/ቤት (በመጅሊሱ የተቋቋመ) ሽፋንነት- ልጅ አባቱን ሊመርጥ!!
ይህንን ዜና ተከትሎ ግንቦት 1 ቀን በአዲሳባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ የ”ነባሩ” እስልምና ተከታዮች (ለ“አህባሽ” በአቶ ሽፈራው ተ/ማሪያም የተሰጠ አዲሱ ለምድ) ብቻ ለጉባዔ ታደሙ፤ መከሩም፤ ዘከሩም፤ በመጨረሻ ላይ የእነ ጨሎ ልጅን ጅማሮ አጠናክሮ የሚቀጥል፤ ድክመታችውን የሚያርም፤ “ጊዜያዊ” የመጅሊስ ፕሬዚዳንት ለመሾም ጠንካራ ታጋይ ማፈላለጉን ተያያዙት፤ ከብዙ ቁፋሮ በኋላ አንድ ጀግና ብቅ አሉ- ከትግራይ ሸህ ከድር ማህሙድ ይባላሉ፡፡
ሸህ ከድር የትግራይ ክልል መጅሊስ ፕሬዚዳንት የነበሩ ሲሆን ከወር በፊት ሚያዚያ 1 ቀን ስልጣናቸውን አስረክበው በታላቅ ሽኝት ለዕድገት ወደ አዲሳባ መጥተው የዑለማዎች ም/ቤት ፕሬዚዳንት አማካሪ በመሆን ተሹመው ለአንድ ወር ያህል ካገለገሉ በኋላ ነው-ትላንት ለ”ጊዜያዊ” የፌዴራል መጅሊስ ፕሬዚዳንትነት የታጩት(“ጊዜያዊ” በመጅሊስ የዘመን አቆጣጠር ገደብ የለውም)፡፡ ከአንድ ወር በኋላም ስልጣናቸውን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል-ምናልባት ህዝበ-ሙስሊሙ ቁሞ ከጠበቃቸው!
ይድረስ ለክቡር አቶ መለስ!
ክቡርነትዎ ሦስቶቹ መሰረታዊ ጥያቄዎቻችንን እደግማቸዋለሁ!
1. የመጅሊሳችንን መሪዎች እኛው፣ ከእኛው፣ ለእኛው፣ በነፃነት፤ በግልፅ፤ ያለማንም ጣልቃ-ገብነት በመሳጅዳችን እንምረጥ!!! ስለዚህ ሚኒስትር ሽፈራው የሚባሉት የርስዎ መንግስት ቱባ ባለስልጣን ‘ጥቁሩን አህባሽ አውርደው “ነጩን አህባሽ” (በራስዎ ቋንቋ የ“ነባሩ እስልምና ዑለማዎች”) እንዳይተኩልን’፡፡ ምክንያቱም ጉልቻ ቢለዋወጥር ወጥ አያጣፍጥምና! ክቡርነትዎ….ሰምተዋል!? መጅሊሱ በስንት አባቶቻችን ደም እንደተመሰረተ በአይንዎ አይተዋል! ደም፤ ህይወት፤ ገንዘብ፤ ጊዜና ጉልበት ተከፍሎበታል……..!
2.
አወሊያም ሆነ ሌሎች የህዝበ ሙስሊሙ ተቋማት እንደመጅሊሱ በብዙ መስዋዕትነትና ትግል የቆሙ ናቸው፤ ስለዚህ ለዚህ ለአዲሱ (ይቅርታ! ለ“ነባሩ” ማለቴ ነው) ሃይማኖት ማጥመቂያም ሆነ ለፖለቲካ ስራ መጠቀም አይቻልም፡፡ ሙስሊሙ እንደሰራቸው
የራሱ ንብረት ሆነው በራሱ ሰዎች ይተዳደሩ!!!
3.
አህባሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1994/5 ጀምሮ በ’NGO’ነት በራሱ ማዕከላት እንደሰበከው ዛሬም መስበክ ይችላል፤ ነገር ግን ተገደንና ተስፈራርተን በሙስሊሙ ህዝብ ተቋማት ውስጥ ያለ አግባብ ሊጫንብን አይገባም፤ ነውርም ነው፤ ኢ-ሰብዓዊም ነው፤ ኢ-ህገ-መንግስታዊም ነው!!
ጥያቄዎቹ አለቁ፤ በቃ አራት ነጥብ(፡፡) አይጨመ(ም)ሩ፤ አይቀነ(ን)ሱ..(‘ጨ’ ና ‘ቀ’ ይጠብቃሉ!)- አራት ወራትን አሳለፉ!!! ስለዚህ ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ጥፋት አይስሩ! ጥቁር ታሪክ አይስሩ!
ይድረስ ለሙስሊም ኢትዮጵያውያን!
ውድ ሙስሊም ወንድምና እህቶቼ፤ እናትና አባቶቼ
ይህ ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄ ትግላችን ከፍተኛው ጡዘት ላይ ደርሷል-በአላህ ፈቃድ! በዚህም ሁለት ጥቁር ነጥቦች መቼም አይረሱንም-የካቲት 26 ፌዴራል ጉዳዮች “መልሶቹ”ን የተፋበት ቀን እና ሚያዚያ 19-የአሳሳ ንፁሃን ሙስሊም ወንድሞቻችን በፖሊሶች ጭፍጨፋ በግፍ ህይወታቸው ያለፈችበት ቀን! (አላህ ጀነትን ያጎናፅፋቸው!)
ስለዚህ፤
1. አሁንም ቢሆን አንድም ጥያቄያችን በአግባቡ አለመመለሱን በማወቅ ለሌሎችም በአግባቡ ማስረዳትና ሴራውን ማጋለጥ ብሎም በትግላችን ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ መስጨበጥ….
2. አንድነታችንን በጠበቀና ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከየመሳጅዳችን ቅጥር ግቢዎች ሳንወጣ የተቃውሞ ድምጾቻችን አጠናክሮ ማሰማት (አደራ ስሜታዊነትን እናስወግድ)
3. ማንኛውም ወገን በሚበትናቸው ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች ሳንረበሽና ራሳችን ለራሳችን የደህንነት ኃይል በመሆን ሰላማዊ ተቃውሞአችንን ሊበክሉ የሚቃጡ ሰርጎ ገቦችን በጥንቃቄ መከታተል፤ መሳጅዶቻችን በንቃትና በትጋት መጠበቅ- ለትልቁ ዓላማችን ወሳኝ ነውና!
4. ወደድንም ጠላንም ይህ ተቃውሞ ላይመለስ 11ኛው ሰዓት ላይ ደርሷል! ይህ ጥያቄ ከተቀለበሰ ትልቅ አደጋ አለው፤ ትልቅም ታሪካዊ ጠባሳ ጥሎ ማለፍም ብቻ ሳይሆን ምናልባት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድጋሜ ላይነሳ ተቀብሮ ሊቀር ይችላል፤ እንደ ቀላል ነገር ካየነው እስልምናን በኢትዮጵያ ውስጥ አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባቱ አይቀሬ ነው፤ ለዚያ ደግሞ ተጠያቂዎቹ እኛው ነን፡፡ ስለዚህ ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን እያዳንዳችን የእስልምና ተሟጋች መሆን ይጠበቅብናል!!
5. መረጃ ኃይል ነው! መረጃን በጊዜው፤ በዕውነተኝነት፤ በአስቸኳይ ለሌሎች ማቀበል ለሰላማዊ ትግላችን ወሳኝ ነው፡፡
6. ለክርስቲያን ወገኖቻችንና ለሌሎችም ኢትዮጵያዊያን የትግላችንን መነሻና እስካሁን የተጓዘበትን ሂደት ማስረዳት አለብን፡፡
7. በምናደርገው ሰላማዊ ተቃውሞ ዙሪያ መጠነ-ሰፊ የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን መስራት አለብን፡፡ ስለዚህ ትዕይንቶችን በድምፅና በምስል በመቅረፅ ወደ ኢንተርኔት መረጃ ቋቶች መስቀል፤ ትዕይንቱንም በፅሁፍና በምስል መለጠፍና ለዜና አውታሮችም ማቀበል…ወዘተርፈ………..
እዚህ ላይ ይብቃኝ፤ ትግሉ ግን ይቀጥላል!!
ድል ለኢስላም ነው!!
አሏሁ አክበር!! አሏሁ አክበር!!
No comments:
Post a Comment