Sunday, June 3, 2012

የሰማዩን እንኳ ተዉልን!


አክመል ነጋሽ (መጋቢት 2004)
    ይኸው ዘጠኝ ወራት ተቆጠሩ-መንግሥታዊ ድጋፍ እየተሰጠው ያለው (state sponsored) የ‹‹አሕባሽ›› አንጃ ነውጡን ከጀመረ! ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ የተዘጉ መስጊዶችን፣ የተከረቸሙ መድረሳዎችን፣ ከሥራ የተሰናበቱ የስግደት መሪዎቻችንን ብዛት ማን ቆጥሮ ይዘልቀዋል? በሐምሌ 2003 ሐረር በሚገኘው የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሕዝባዊ እውቅናን ከተነፈገው መጅሊስ ጋር በመተባበር አዘጋጅቶት ከነበረው የ‹‹አሕባሽ›› የማጥመቂያ ‹‹ሥልጠና›› በኋላ ብዙ ነገሮች ተለዋውጠዋል። በ‹‹ሥልጠና››ው ወቅትና ከዚያም ቀደም ብሎ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከመጅሊስ አመራር አባላት ጋር የተማማሉበትን ‹‹አሕባሽ››ን በኢትዮጵያ የማንገሥ ቅዠት እውን ለማድረግ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያልተፈነቀሉ ድንጋዮች አልነበሩም። እኛ በሚፈነቀሉት ድንጋዮች ላይ ረዣዥም የመንግሥት እጆች ይታዩን ነበር።
    መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን የሚደነግገው የሕገ-መንግሥቱ አሥራ አንደኛ አንቀጽ አንዳንዴ የወረቀት ነብር ይመስለኛል። ምንም እንኳን አንቀጹ እና በውስጡ ያሉት ንዑሳን አንቀጾች በማያሻማ መልኩ የመንግሥትንና የሃይማኖትን መፋታት ቢያውጁም በተግባር ግን ፉርሽ ናቸው። የኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ በስፋት እንደሚያምነው የመጅሊሱን የአመራር ቦታዎች (በተለይም ከ 1987 ወዲህ) ከመደልደል ጀምሮ አሁን ትልቅ ውዝግብ እየፈጠረ እስካለው የ‹‹አሕባሽ›› አጀንዳ ድረስ መንግሥት ዋነኛው ተዋናይ ሆኖ ታይቷል። በመጅሊሱ የአመራር ወንበሮች ላይ ከተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ያለምርጫ ግለሰቦችን የሚያስቀምጠው መንግሥት መሆኑን ሕዝቡ የተመለከተባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች ተከስተዋል። ‹‹ሰፊውን የኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ ይመራል›› በሚባለው መጅሊስ ውስጥ የውሳኔ ሰጪነትን ሚና የሚወጡ ሥውር እጆች የመንግሥትን ቀጥተኛ ትእዛዝ ለማስፈጸም የተዘረጉ ናቸው። ለዚህም ነው ተቋሙ ለተቋቋመለት ዓላማ የሚሆን አንድም ቁም ነገር ሳይሠራ ሁለት አሥርት ዓመታትን የዘለቀው። መጅሊሱ ‹‹እመራዋለሁ›› በሚለው የሕዝብ ብዛት ተመርኩዞ ሊያከናውናቸው ይገቡ የነበሩ አያሌ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ሕልም ብቻ ሆነው ቀርተዋል። አንድ ኢስላማዊ የሃይማኖት ተቋም መስጊድ ካልገነባ፣ የሃይማኖት ትምህርት ቤት ካላነፀ፣ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ካላሳተመ ምን ቁም ነገር ‹‹ሠራ›› ብለን እናወራለታለን? የኛ መጅሊስ ከነዚህ ሁሉ የለበትም፤ ምክንያቱም ለሿሚዎቹ ለማደግደግ እንጂ ሕዝበ ሙስሊሙን ለማገልገል ጊዜውም ሞራሉም የለውምና! ይህ ሁሉ የጣልቃ ገብነት ጣጣ ነው።
   በሽፍንፍን ለዓመታት ቆይቶ የነበረው የመንግሥት-መጅሊስ ጋብቻ (በሌላ አነጋገር የመንግሥት ጣልቃ ገብነት) አሁን ይፋ ወጥቷል። በተለይም ከ 2003 ወዲህ ‹‹አክራሪነትን ለመዋጋት›› በሚል ሰበብ (pretext) ሁለቱ ወገኖች የምድሩን የወሰኑልን ሳይበቃቸው የሰማዩንም መንገድ ሊመትሩልን ወደ አደባባይ ብቅ ብለዋል። ‹‹አክራሪነትን ለመዋጋት›› ፌዴራል ጉዳዮችና መጅሊስ ‹‹አሕባሽ›› በሚባል ስል መጥረቢያ ‹‹ወሐቢያ›› ብለው የሠየሙትን ባሕር ዛፍ ለመገንደስ ጥረት ማድረግ የጀመሩት ከዚህ ወቅት ጀምሮ ነው። ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የወደቀ ዛፍ ባይመለከትም ዛፉን ለመገንደስ ከፍተኛ በጀት የተመደበላቸው ትላልቅ ‹‹ሥልጠና››ዎች በሁለቱ ወገኖች አማካኝነት ተዘጋጅተው በርካቶች በግዳጅ እንዲሠለጥኑ ተደርገዋል።
    በ‹‹ሥልጠና››ዎቹ ላይ የተገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ያለምንም መሳቀቅ በሃይማኖት ጉዳይ ገብተው ሲፈተፍቱ ታይተዋል። ይህ ሃይማኖታዊ ‹‹ሥልጠና›› ወይም አንዱን ሙስሊም በሌላው ሙስሊም ላይ የሚያነሣሣ ዘመቻ ያዘጋጀው መንግሥት መሆኑንም ነግረውን አድምጠናል። ይህም ብቻ ሳይሆን ‹‹ሥልጠና››ው ገና በስፋት እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል። ለተገኙት ሠልጣኖች ንግግር ያደረጉ አንዳንድ ባለሥልጣናት ከዚህም ብሶ ማን ትክክለኛ ሙስሊም፣ ማንስ ደግሞ ሓሳዊ ሙስሊም እንደሆነ ‹‹መጽሐፉን ገልጠው›› ነግረውናል። ከሃይማኖት ልሂቃን እና ከሃይማኖት አንጃዎች የትኛው ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ የተሸለ እንደሆነ ‹‹ኪታብ ገልጠው›› መስክረዋል። ከዚህም በከፋ መልኩ ሌሎቹ ቅንጅትና ኢሕአዴግ አብረው መደራደር የማይችሉትን ያህል ይኸኛው ሙስሊም ከዚያኛው ሙስሊም ጋር በፍጹም አብረው ሊሆኑ እንደማይችሉ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የተባለ ‹‹ድርሳን እየገለጡ›› አስረድተውናል። ባለሥልጣናቱ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ የፖለቲካ ማሊያቸውን ለብሰውና ሚዲያም ጭምር ጋብዘው ነው። እንዲህ ሁሉ ሆኖ አባላቱም ጭምር በጣልቃ ገብነት ወቅሰውት መንግሥት እኔ ጣልቃ አልገባሁም እያለ ነው። ከዚህ የተሻለ ከቶ ምን ዓይነት ጣልቃ ገብነት ይኖር ይሆን?
   ባለሥልጣናቱ ከዐራት ኪሎ መስጊድ ድረስ ያመጣቸው አዲስ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ባይኖርም አዲስ የፖለቲካ ስትራቴጂ መኖሩን ግን ማሽተት ይቻላል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋስኦ (Discourse) ውስጥ ሃይማኖት ሁሌም ሁነኛ ቦታ አለው። የዐራት ኪሎ ሰዎች ግን እስካሁን በደንብ እንዳልተጠቀሙበት የገባቸው አሁን ሳይሆን አይቀርም። አሁን ተረኛው ተመዛዥ ካርድ ሃይማኖት ሆኗል። አሁን ግን ይህ የተመዘዘ ካርድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሳያመዝን አልቀረም። እኔ እስከሚገባኝ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር ክብሩንና ሌሎች ምድራዊ እሴቶቹን ለሌላ ምድራዊ ጥቅም ብሎ አሳልፎ ይሰጥ ይሆናል። ለምድራዊ ዓላማ ብሎ ግን እምነቱን ቤዛ የሚያደርግ እምብዛም ይኖራል ብዬ አላምንም። ለዚህም ነው መንግሥት የጀመረው ስትራቴጂ ‹‹ብዙም አያዋጣም›› ብዬ የምሞግተው። ያም ሆኖ ግን መንግሥት አሁንም እምነት በጣለባቸው ልማታዊ ‹‹ሼኾች›› አማካኝነት አብዮታዊ ዴሞክራሲን እየሰበከ ነው።

የሥርዓቱ ወይስ የአምላክ ሎሌዎች?
     ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ‹‹ይመራናል›› ብለው ያቋቋሙት ተቋም (መጅሊስ) ባለፉት አሥራ ሰባት ዓመታት ከሼኽነት ይልቅ የካድሬነት መለዮ ለብሰው በሚጫወቱ መሪዎች ሲተዳደር ቆይቷል። እነዚህ አመራሮች በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ ሁሌም ‹‹እንመራዋለን›› ለሚሉት አማኝ አንዲት ቁም ነገር ከመሥራት ይልቅ ሥልጣናቸውን ለርካሽ ፖለቲካዊ ተግባር ሲያውሉት ዐይተናል። አመራሮቹ ከሚመሩት ሕዝብ ይልቅ ወንበሩ ላይ ላስቀመጧቸው ረዣዥም የመንግሥት እጆች ሲያጎበድዱ፣ የነዚህኑ እጆች አቅጣጫ እየተከተሉ ጎንበስ ቀና ሲሉ ታዝበናል። ወደሥልጣን ያመጣቸው እጅ ከሥልጣናቸው ለማውረድም ብዙ እንደማይቸገር ስለሚረዱ የሱን የልብ መሻት ለመሙላት ለሶላት ለተገኘው ሕዝብ መለኮታዊ ቃል ነግሮ መንፈሳዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ይልቅ የ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲን›› እና የመንግሥተ-ዐራት ኪሎ ‹‹ቅዱሳን መጽሐፍት››ን እየገለጡ ያነበንባሉ። ዘወትር ከስግደት በኋላም ‹‹የመንግሥተ-ዐራት ኪሎ መንግሥት ትመንደግ!›› እያሉ ጌታን ይለማመናሉ። ምርጫ ሲቃረብ ደግሞ እነዚሁ ጠምጣሚ ካድሬዎች ሥልጣን ላይ ያስቀመጣቸውንና ያከረማቸውን ረዥም እጅ እያመሰገኑ ‹‹ምእመን ሆይ! ይህን ባለ ረዥም እጅ መምረጥ መንግሥተ ሰማያትን ያስወርሳል!›› ሲሉ ይሰብካሉ። ሥርዓቱ የፈጠራቸው የሼኺ ሎሌዎች እነዚህ ናቸው።
     ኢማም አል ገዛሊ የተባሉ የመካከለኛ ዘመን ልሂቅ ‹‹ሃይማኖታዊ እውቀት ምድራዊ ክብር ማግኛና የሥልጣን ማደላደያ መሣሪያ በሚሆንበት ዘመን ይህንኑ ክብር ሽተው ሃይማኖታዊ እውቀት የሚማሩ ሰዎች ቁጥር ያሻቅባል›› ብለው ጽፈው ነበር። አሁን በዚህ ዘመን ያለው እውነታም ይኸው ይመስለኛል። ልማታዊ ሼኺዎች ቅዱስ የሆነውን የአምላክ መንገድ ርካሽ ፖለቲካዊ ቁማር ማሳኪያ ሊያደርጉት ላይና ታች ሲንከላወሱ ማየት የተለመደ ነው። የሃይማኖት አባት ሲባል ፍትሕ እንዲሰፍን፣ አብሮነት እንዲጸና፣ ቀናው የአምላክ መንገድ እንዳይዛነፍ ሌት ተቀን የሚጥር መሆን ነበረበት። አንድ የነቢዩ ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) ንግግር ‹‹ከትግሎች ሁሉ ምርጡ በአምባገነን መሪ ፊት እውነትን መናገር ነው!›› ይላል። የኛ የሃይማኖት አባቶች ግን ፍትሕ ሲጓደል፣ መብት ሲጣስ፣ ሃይማኖት ሸቀጥ ሲሆን ከመንቀፍ ይልቅ የሥርዓቱ ሎሌዎች ሁነው የአምላክን መንገድ ይሽራሉ። ‹‹አፍንጫ ሲመታ ዐይን ያለቅሳል›› እንዲል ብሒሉ የዘንድሮ ‹‹ሼኾች›› ዐራት ኪሎ ጉንፋን ሲይዘው መስጊድ ውስጥ ሆነው ያነጥሳሉ።
    ልማታዊ ሼኾች… እስቲ እንጠይቃችሁ… መጽሐፉ የሚለው ይህንኑ ነው? መጽሐፉ የሚያስተምረው ስለእውነት ማደርን እንጂ ለምድራዊ ጥቅም ብሎ ሃይማኖት መሸጥን አይደለም። የአምላክን ቃል ከፍቶ ማስተማር እንጂ ጋዜጠኛ ሰብስቦ፣ ካሜራ አስደግኖ የፈርዖንን የቅጥፈት እንቶ ፈንቶ ማነብነብ አይደለም ጀነትን የሚያስወርሰው። ከመጠምጠም ማወቅ ይቅደም!
    እነዚህ የምድሩን ጨርሰው የሰማዩንም ፈረስ ሊፈናጠጡ የከጀሉ ጠምጣሚዎችና የዐራት ኪሎና የመጅሊስ መቀያየጥ ጉዳይ ሰላም የነሣቸው በአዲስ አበባና በክልል የሚኖሩ ሙስሊሞች ‹‹ኧረ የፍትሕ ያለህ!›› እያሉ መጮህ ከጀመሩ ይኸው ሦስት ወራት ተቆጥረዋል። መንግሥትም ‹‹ከደሙ ንጹህ ነኝ!›› እያለ በተገኙት ሚዲያዎች ሁሉ ሐሳቡን እያስተጋባ ነው።
     ሕዝቡ ብሶቱን እንዲያሰሙለት የመረጣቸው አሥራ ሰባት ተወካዮች ባለፈው የካቲት 26 ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መልስ የሚመስል ‹‹መልስ›› ተሰጥቷቸዋል። ሕዝበ ሙስሊሙ ጠምጣሚዎቹ ካድሬዎች ከሥልጣን እንዲነሱለትና ሕዝባዊ ምርጫ እንዲካሄድ ላቀረበው ጥያቄ ያገኘው ምላሽ ብዙም አዎንታዊ አይደለም። የፌዴራል ጉዳዮች መልስ በደምሳሳው ‹‹ለመጅሊሱ የአመራር ቦታዎች ምርጫ ይደረጋል›› ከማለት በዘለለ ‹‹መቼ?›› እና ‹‹እንዴት?›› ለሚሉት ጥቄዎች የሰጠው ምላሽ የለም። አላዋቂ ጠምጣሚዎቹ የመጅሊስ አመራሮች በበኩላቸው ‹‹ምርጫውን ብር ካገኘን እናካሂዳለን፤ የምርጫ መመሪያውን እያዘጋጀን ነው›› በማለት ሙስሊሙ ሳይመርጣቸው ወንበሩ ላይ መቀመጡ ሳያንሳቸው ምርጫውንም በቆሸሸ እጃቸው እንዳይሆን ሊያደርጉት ተዘጋጅተዋል። ይህ ሁኔታ ክፉኛ ያበሳጫቸው ከ500 ሺህ በላይ የከተማዋና የክልል ሙስሊሞች ባለፈው ሳምንት አሥረኛውን የተቃውሞ ጁሙዓ በአወሊያ አካሂደዋል።
    በሕዝብ የተነሱት ሌሎቹ ጥያቄዎችም እንዲሁ ከመንግሥት በኩል አዎንታዊ ምላሽ አላገኙም። ከገጠር እስከ ከተማ በግዳጅ ሲሰጥ የነበረው የ‹‹አሕባሽ›› ‹‹ሥልጠና››ም እንዲሁ ምንም ዓይነት ግዳጅ እንዳልነበረበት እነዚሁ ከኮሚቴዎቹ ጋር የተገናኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሞግተዋል። ይህን የመንግሥት ምላሽ ባለፈው ሳምንት አወሊያ ተገኝቶ ያደመጠው ሕዝበ ሙስሊም ንዴቱን በሚገባው መልኩ ገልጿል። ጥያቄዎቹ በአግባቡ እስኪመለሱ ድረስም ሰላማዊ ተቃውሞውን እስከመጨረሻው እንደሚቀጥል ቃል ገብቷል። አሥራ ሰባቱ ተመራጮች ጥያቄያቸውን ለሌሎች የመንግሥት ፍትሕ ቢሮዎች እስከ ጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ድረስ ለማቅረብ እንቅስቃሴ ቢጀምሩም ከባለፈው ሳምንት መባቻ ጀምሮ የመንግሥት ደህንነቶች መላወሻ አሳጥተዋቸዋል። ከሰባት በላይ የደህንነት መኪኖች የኮሚቴውን አባላት ከጠዋት እስከማታ በመከታተል እና በማዋከብ ላይ ናቸው። የሕዝብን ሰላማዊ ጥያቄ በሰላማዊ መልኩ ለመንግሥት እያቀረበ ያለን ቡድን ይህን ያህል ማዋከብ ትርፉ ምን እንደሆነ አልገባኝም።
    ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የጠየቃቸው ጥያቄዎች ሕገ-መንግሥታዊ በመሆናቸው መንግሥት ‹‹ጣልቃ አልገባሁም›› እያለ መደባበቁን ትቶ ትክክለኛውን ምላሽ ለሕዝብ ሊሰጥ ይገባል። የምድሩን ትተንላችሁ ሁሉም በእጃችሁ ሆነ፤ የሃይማኖት ነጻነት ጥያቄያችንን እንኳ መልሱና የሰማዩን መንገድ ተዉልን!

No comments:

Post a Comment