Thursday, October 4, 2012

ግልጽ ደብዳቤ መልስ በተነፈገው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ ዙሪያ


ሰኢድ ሁሴን መሀመድ - ሰሜን አሜሪካ
መስከረም 18, 2005 ዓ.ል.

http://badrethiopia.org/

ግልጽ ደብዳቤ

ለተከበሩ የኢ ፌ ድ ሪ ጠቅላይ ሚንስቴር
ኣቶ ኃይለማርየም ደሳለኝ
አ አ

ለተከበራችሁ የኢህኣዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሎች
ባላችሁበት፣

ጉዳዩ: መልስ የተነፈገው የኢትዮጵያ ሙስልሞች ጥያቄን ይመለከታል

ለተከበራችሁ የሃገራችን መሪዎች፤

ይህንን አሳሳቢና አስቸኳይ ጉዳይ አስመልክተን አቤቶታችንን በአክብሮትና በቅን መንፈስ ስናቀርብ፤ዓላማችን ለሃገራችንና ለህዝባችን ካለን ጽኑ ፍቅር በመነሳሳት እንጂ ምንም አይነት የፖለቲካ ተልዕኮ እንደሌለን በቅድምያ ልናስታዉቃችሁ እንወዳለን።

አመት ሊያስቆጥር ወራት የቀሩት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ እነሆ እስከ አሁን ሰሚ አጥቶ ወደ አላስፈላጊ እርምጃና ክስ መቀየሩ ለማንም ግልጽ ነው ብለን እናምናለን፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊም ምዕመናን በመላው ሃገሪቷ ውስጥ ባሰሙት የተቃውሞ ድምጽ፤ የእስላምና ሃይማኖት ከመጤው የኣህባሽ አመለካከት ነጻ ሆኖ እንዲቆይ መልሰው መላልሰው ለመንግስት አቤቶታ ቢያቀርቡም እስከ አሁን የሰማቸው የመንግስት አካል አለመኖሩ እጅግ በጣም አሳዝኖናል። መንግስታችን አቤቶታችንን በቅን ይረደዋል ብለን በመተማመን በትዕግስት ለወራት በሰላማዊ መንገድ ብንቀሳቀስም፣ የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖልሶች የተሳሳታ መረጃ በመሰብሰብ በወሰዱት እርምጃ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት እጅግ የከፋ መሆኑን መስርያ ቤታችሁ ያውቃል ብለን እንገምታለን።

ህገ መንግስቱ ያጎናጻፋዉን መብቱን በተሟላ መንገድ ለማስከበር የጀመረውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ስረዓት አልባዎች እንዳይተናኮሉት ሙስሊሙ ህብረተሳብ ያደረገው ከፍተኛ ጥንቃቄ በመንግስት አመለካካት የሚያስመሰግነዉ እንጂ የሚያስደበድበው አልነበረም። በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ሰልፈኛ በመንግስትም ሆነ በህዝብ ንብረት ላይ አንዳችም ጠጠር ሳይወረዉር ህግን አክብሮ አቤት ድምጻችን ይሰማ ብሎ መወትወቱን የሃገራችን መንግስት በቅን ልቦና ሊገነዘበዉ የሚገባ መልዕክት ነው ብለን እናምናለን። ይህ ህዝባዊ ትግል በሰላማዊ መንገድ ግቡን እንዲመታ ከመንግስት አካላት ጋር እንድንወያይና ለተነሱት ጥያቄዎችም መልስና መፍትሄ ለማስገኘት አመቺ ሁኔታ እንዲፈጥር አስራ ሰባት አባላት ያለው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በብዙ መቶ ሽህ ምዕመናን ድምጽ በአዲስ አበባ ተመርጦ ነበር።

ይህ ኮሚቴ በውጭና በሀገር ውስጥ ባሉ ምእመናን የድጋፍ ድምፅ አግኝቶ ለወራት ከከፍተኛ የመንግስት በለሥልጣኖች ጋር ሲወያይ ከቆየ በሗላ በመጨረሻም አባሎቹ ለእስር መዳረጋቸው መላውን የሙስሊሙን ህዝብ እጅግ በጣም ያሳዘነና ያስቆጣ ድርጊት ሆኗል። እነዚህ ምሁራንና ሽማግሌዎች ያላንዳች ፍርድ እስካሁን በእስር መሰቃየታቸው የሁላችንንም ልብ አቆስሏል፤ የነርሱን ቤተሰቦች ኑሮ አዛብቷል። እውነቱን ለመናገር ከተፈለገ እነዚህ የኮሚቴ መሪዎች ብርቅዬ የሀገሪቷ ልጆች ናቸው። የሚያከብሩትና የሚወዱት መንግስታቸው የዚህ አይነት እንግልት ይደርስብናል ብለው አልገመቱም። ከውጪ እንደምንሰማው ከሆና በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው ነው ይባላል።

ክቡራትና ክቡራን የሐገራችን መሪዎች

የራስን ወገን የሆኑ ሀገርን የሚያኮሩ ውድዬ ዜጎችን ባልፈጸሙት ወንጀል ለስቃይና ግርፋት አሳልፎ መስጠት ለህሊና የሚከብድ ድርጊት ነው። በታሪክ ፊትም ማስወቀሱ አይቀሬ ነው። ህግን የተገዙ ዜጎችን ህግ ከሚጥሱ ወንጀለኞች እኩል ማዋረድና ማጎሳቆል የአዕምሮ ቁስል ነው። በመንግስት የዜና ማሰራጫዎች እንደሚወራው ከሆነ የሙስሊሙ እንቅስቃሴ የአንዳንድ አክራሪዎችና ሽብርተኞች ሴራ ነው ይባላል። ሀቁ ግን ከዚያ የራቀ ነዉ። የሚሊዮኑ ህዝብ ጥያቄ እንደ ጥቂት ግለሰቦች ፍላጎትና ጥያቄ ተደርጎ መወሰዱ ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ታላቅ ሀዘን ነው።

ክቡራትና ክቡራን የሐገራችን መሪዎች

በሙስሊሙ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ በመሳተፍ ያለዉ ሚሊዮኑ ህዝብ አሸባሪ ከሆነ ሀገሪቷም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለሆነች ሁላችንንም የሚያሳጋ ጉዳይ ሆኗል ማለት ነዉ። እውነታው ግን እንደዚያ አይደለም። የሙስሊሙ ህዝብ ጥያቄ በዘመኑ የማስፈራሪያ መፈክር ተሸፍኖና ተድበስብሶ እንዲቀር የሚፈልጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዳሉ ለኛ ግልጽ ነው።እነዚህ አካሎች ለመንግስት የተሳሳተ መረጃዎችን በማቅረብ የሌለ ስጋት ፈጥረው ሰለማዊው እንቅስቃሴ ወደ ሁከት እንዲያመራ በመጣር ላይ ናቸው። መንግስት ይሄንን ሴራ በጥሞና እንድያጤነው በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።ሙስሊሙን ህዝብ ከመንግስት ጋር ለማጋጨት ተደረጅተው የሚንቀሳቀሱ የአህባሽ አባሎች በሀገራችን ውስጥ ብጥብጥ ለመፍጠር ሌትና ቀን በመራወጥ ላይ ለመሆናቸዉ ተግባራቸዉ ምስክር ነው። በመሆኑም የጠቅላይ ሚንስቴሩ ቢሮና የእህኣዴግ አመራር በአስቾኳይ ልዩ መርማሪ ኮሚቴ ሰይሞ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶት አንድ እልባት እንድያደርግለት በአክብሮት እንጠይቃለን።

ይህ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ፈሩን ሳይስት ግቡን እንዲመታ መላው የሙስሊሙ ህዝብ ታላቅ ጥንቃቄ በማድረግ ላይ ቢሆንም መንግስት በሀይል ተመክቶ በመውሰድ ላይ ያለው እርምጃ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ትክክለኛው መፍትሔ ህጋዊና ድሞክራሳዊ መልስ ብቻ ነው።

ውድ የተከበራችሁ የሀገራችን መሪዎች

አህባሽ የተባለውን ቡድን አስመልክቶ ህዝበ ሙስሊሙ ያለውን ዕይታ እስቲ በምሳሌ እንጠቁማችሁ። በክርስቲያኑም ውስጥ የተለያዩ አመለካከት ያላቸው የሃይማኖት ዘርፎች እንዳሉ ሁሉ፤ በእስልምና ውስጥ መኖራቸው አይካድም። አህባሽ ግን በዚሁ ቅርብ ዓመታት የመጣ ፈሊጥ እንጂ ከቀድሞ የነበረ ዘርፍ አይደለም። ሆኖም የመኖርና የመስፋፋት መብቱ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን ድኃው ህዝብ ጥሮ ግሮ ባሰረው መስጊድ ላይ በመንግስት ድጋፍ አባት ልሁን ማለቱ በእውነቱ አይን ያወጣ ዘረፋና ወረራ ነው። ታድያ ምሳሌውን ለመደምደም የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ምዕመናን የሚፀልዩበትን ቤተክርስቲያን የመንግስት ኃይል መጥቶ “ከዛሬ ጀምሮ ከሮማው ጳጳስ የተላኩ የካቶሊክ ካህን መሪያችሁ ሆኖ እንዲሰሩ መድበንላችኃል” ቢባሉ ምን ይሰማቸው ይሆን? የኢትዮጵያ ሙስሊምን የገጠመው መሰናክል በርግጥ ይህንን የሚመስል ነው።

ጉዳዩ ሃይማኖትን የማክረርና ሌላውን ቡድን የመጥላት ዘመቻ ሳይሆን፤ “በመስጊዳችን እኛው መሪያችንን እንምረጥ፤ ከአንድ ሺህ አራት መቶ ዓመታት በላይ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ሃይማኖታዊ ግንዛቢያችንን ይዘን መሄዱ ይፈቀድልን፤ አህባሽ በስልጠና ስም የሚያስተምረን አዲስ ነገር የለምና መንግስት የሀገሪቷን ገንዘብ ለዚህ አያበክን! በአህባሽ አንጠመቅምና እባካችሁ ተውን!” እያለ የሚጮኸዉን ህዝብ መንግስት ለምን አይሰማም? የውጭ ሀገር ጫናም ካላ፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሁኔታ ልዩ መሆኑን አስረዷቸዉና የሱማሌያውን ዓይነት አክራሪነት ፈርተው ህዝባችን ከመጮቆን እንዲቆጠቡ እባካችሁ ንገሯቸውና ሀገሪቷን ከብጥብጥና ሁከት አድኗት።

ይልቅ አሸባርዎችና አክራርዎች ይህንን ሃይማኖታዊ ብሶት መሣሪያ አድርገው በምዕመናን ውስጥ ሠርገው ገብተው ሰላማዊውን እንቅስቃሴ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይወስዱ መንግስት የሙስልሙን ህዝብ ጥያቄ በፍጥነት ቢመልሰው ለሀገር ይበጃል። ከዚያም በማስከተል የአከባቢ ባለስልጣናት ከምዕመናኑ መሪዎች ጋር በመመካከር ህዝቡን እንዲያረጋጉ ቢደረግ መልካም ይመስለናል። በተለይ በእስራትና በግርፋት የተዋከቡ ወጣቶች ለመጥፎ ተግባር እንዳይጋለጡ የመንግስትና ህዝባዊ ድርጅቶች በምዕመናኑ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የተሃድሶ ምክር ቢለግሱ አይከፋም። ነገር ግን ከሁሉም በላይ ህጋዊና ሠላማዊ መልስ እንጂ እስራትና ግርፋት እንደመፍትሄ መቆጠሩ ቢቆም ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል ብለን እናምናለን።

የተከበራችሁ የሀገራችን መሪዎች

በእውነቱ መፍትሔው በእጃችሁ ነው። ሙስሊሙ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ሌላ ትርጉም እስካልተሰጣቸው ድረስ ግልጽና ቀላልም ናቸው።
፩ኛ፡ “የመጅሊስ አመራር ወርዶ ህዝብ በሚመርጠው ተወካዮች ይተካ፤ ፪ኛ፡ እስላማዊው ተቋም አወልያ በህዝብ በሚመረጡ የቦርድ አባሎች ይተዳደር፤ ፫ኛ፡ ከባህር ማዶ በቅርቡ የመጣው የአህባሽ ቡድን አመለካከት በመንግስት ድጋፍና ሀይል በሙስሊሙ ላይ መጫኑ ይቁምልን!” የሚሉ ናቸው። እስቲ ከነዚህ ጥያቄዎች መንግስትን የሚነካው የትኛው ነው? "አሸባሪ" የሚያሰኘውስ የትኛው ጥያቄ ነው?

በእስላም ሃይማኖት ላይ የግል ጥላቻ ያላቸው ወገኖች የሚሰጡት አሳሳች ትርጉም ተወግዶ፤ መንግስት በአፋጣኝ ህጋዊና ሰብዓዊ መብትን ባሟላ መልኩ ለሙስልሙ ህዝብ አቤቶታ ተገቢውን መልስ እንዲሰጥ እኛም በውጪ ያለነው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በቅን ልቦና እንጠይቃለን። በመጨረሻም: ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስተራችን መልካም የስራ ዘመን፤ ለሀገራችን ህዝቦች ደግሞ ሰላም፤ ደስታና ብልጽግና በመመኘት፤ የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች በፍቅርና በመከባበር በጋራ የሚኖሩባት ኢትዮጵያችንን ፈጣሪ አምላካችን እንዲጠብቅልን እንጸልያለን።

ከልባዊ ሰላምታ ጋር

ሰኢድ ሁሴን መሀመድ
saeedhuseen2001@gmail.com
 በሰሜን አሜሪካ
ጉዳዩ ያሳሰባቸው ኢትዮጵያዊያን ሙስልም ምሁራንና ምዕመናን
(ግዜያዊ ተጠሪ)

1 comment:

  1. Njmcdirect official solves this problem for you. It is an online portal wherein you can submit you’re fine amount

    ReplyDelete