ጃዋር ሙሐመድ
(Translated by Isaac Eshetu)
በኢትዮጵያ መንግሥትና በሙስሊም የመብት ንቅናቄ መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ፍጥጫ ለመተንተን ብዙ ተሞክሯል።
የንቅናቄ አራማጆቹ መንግሥት ከውጭ ያመጣውን የሃይማኖት ቀኖና በግድ በመጫን በሃይማኖታቸው ጣልቃ እየገባ እንደሆነ
እየተናገሩ ነው። መንግሥት ደግሞ በበኩሉ የፍጥጫው ምንጭ ‹‹አክራሪነት›› እና ከአገሪቱ ውጭ ያሉ አካላት እጅ
እንደሆነ እየገለጸ ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሃይማኖትን ለፖለቲካዊ ጥቅማቸው እያዋሉት እንደሆነ እየተናገረ ነው።
ተቃዋሚዎች ደግሞ በተቃራኒው መንግሥት ሃይማኖትን ለ‹‹ከፋፍለህ ግዛ›› መርሁ እያዋለው እንደሆነ
ይናገራሉ።‹‹የትኛው ትክክል ነው?›› ነው የሚለውን ልተወውና ሌላ የበለጠ አንገብጋቢ ጥያቄ ላንሳ… ‹‹የውስጥም
የውጪም የፖለቲካ ሥራ ፈጣሪዎች (political entreprenuers) ከስትራቴጂያዊ ዓላማቸው ፍሬም ሥር ቀርፀው
ለመጠቀም እየተሻሙበት ያለው የሙስሊሙ ኅብረተሰብ እያደገ የመጣ ፖለቲካዊ ንቃት እና ንቅናቄ እንዴት ሊከሰት ቻለ?
ክስተቱን ሊያብራሩ የሚችሉት ምክንያቶች ዐራት ናቸው። አንደኛ፡- በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ እየተፈጠሩ የነበሩት
ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ለውጦች የተሻለ ተሳትፎና ፖለቲካዊ ውክልናን የግድ የሚፈልጉ መሆናቸው። ሁለተኛ፡- ባለፉት ሁለት
አሥርት ዓመታት ኢስላማዊ መነቃቃት (revivilism) በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ። ሦስተኛ፡- መንግሥት እኒህን
ለውጦች ለማስተናገድ የሚችል ከባቢ በድርጅታዊ መዋቅሮቹና ከሕዝቡ ጋር በሚያገናኙት መዋቅሮች ባለመፍጠሩ። ዐራተኛ፡-
የመንግሥት ፖሊሲዎችና ታክቲካዊ አካሄዶች የኢስላማዊ ተቋማትን ነጻነት ያዳከሙ በመሆናቸው፤ በዚህም ሙስሊሙ
ማኅበረሰብ ቅያሜ ውስጥ በመግባቱ።የእነዚህ ዐራት ዋነኛ ምክንያቶች የእርስ በርስ መሥተጋብር ሰፊ ሃይማኖታዊ
መነቃቃትና ፖለቲካዊ ንቃተ-ሕሊናን ፈጥሯል። እስቲ ዐራቱንም ምክንያቶች ሰፋ አድርጌ ለመተንተን ልሞክር።
1. 1. ሙስሊሙበኢትዮ
ጵያፖለቲካውስጥየነበረውዝቅተኛተሳትፎናውክልና
በቀደመው ታሪክ እስልምና በፖለቲካና በሃይማኖት ጭቆና ሥር ሲያልፍ የቆየ ቢሆንም እንደ አስተሳሰብ ወይም ማንነት
ሆኖ ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማደራጃነት (mobilization) የዋለበት ጊዜ እምብዛም አልነበረም ማለት ይቻላል።
በሌላ አነጋገር ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ፖለቲካ የነበራቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነበር እንደማለት ነው። ሙስሊሞች ዛሬም
እንኳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሽ ያህል ቢሆኑም በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል ያላቸው ውክልና እጅግ ዝቅተኛ ነው። ለዚህ
ምክንያት የሆኑ ሦስት ነገሮች አሉ፡-
ሀ/ ከአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀም
ሮ ዋነኛ የፖለቲካ
አሰላለፍ ማዕከል የነበረው ሃይማኖታዊ ማንነት በዘውጌ ብሔርተኝነት ተተካ። በክርስትያን መንግሥታትና በሙስሊም
ሡልጣኔቶች መካከል የተደረገው ከፍተኛ ፍልሚያ ካከተመ በኋላ በክርስትያኑ መንግሥት እምብርት ላይ የኦሮሞ ሕዝብ
መነሣት ግጭቱን ከሃይማኖታዊ ማንነት ይልቅ ብሄርተኝነት ላይ እንዲመሠረት አድርጎታል። በሁለተኛነት ደግሞ እስልምና
ቀስ በቀስና ሰላማዊ በሆነ መልኩ በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ከተስፋፋ በኋላ ቀድመው ከነበሩበት ባህሎችና ተቋሞች
ጋር በመዋሃዱ ገኖ የወጣ ማንነት ከመሆን ይልቅ የባህሉ አንድ አካል እንዲሆን አድርጎታል። በሦስተኛ ደረጃ
የዘውዳዊውን ሥርዓት ለማስፋፋት ወደደቡብ የተደረጉት የማዕከላዊ መንግሥት ወረራዎች ወደ መጨረሻ አካባቢ ሃይማኖትን
በግድ የማስለወጥ ባሕሪያቸውን መቀየራቸውም ከሃይማኖታዊ ማንነት ይልቅ ብሔርተኝነት ላይ ያተኮረ ቅየራ
(assimilation) እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ራስን የመከላከሉ ትግልም አደረጃጀቱን
ከሃይማኖታዊ ማንነት ወደ ብሔር ማንነት ቀይሯል። አጼዎቹ ኃይላቸውን አንድ አድርገው ለማጠናከርና የግቦቻቸውንም
ተገቢነት ለማሳመን ቤተ ክርስትያንን የተጠቀሙ ቢሆንም እስልምና የተወራሪ ብሔሮችንም ሆነ ክልላዊ ቡድኖችን
የሚያስተሳስር መሆኑ የብሔሮቹን አንድነት ለመጠበቅ ሲባል ለሃይማኖታዊ ልዩነት የሚሰጠው ትኩረት ቀንሷል። በመሆኑም
ሃይማኖትን በተመለከተ ብቻ የሚፈጸሙ ጭቆናዎች ራሳቸው የትግል ፉካቸው ብሔርተኛ አደረጃጀት እየሆነ በመምጣቱ
ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ንቅናቄ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል እየጠበበ መጥቷል።
ለ/ ሙስሊሙ በዋነኝነት
ተሠማርቶባቸው የነበሩት ሞያዎች፣ በተለይ ደግሞ ንግድና አርብቶ አደርነት ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር የሚያጋጩ
አልነበሩም። በገጠራማ አካባቢዎችና በሰሜን ሙስሊሞች በጥቅሉ በንግድ ሥራ ነበር የሚሠማሩት። ንግድ ደግሞ ፖለቲከኞቹ
እና መሳፍንቱ የማይመርጡት የተገፋ ሥራ ስለነበር ሙስሊሙ ያለተፎካካሪ ዘርፉን እንዲቆጣጠረው ሆኗል። በሌላ
አነጋገር ንግድ ለሙስሊሞች ተስቦ ወደላይ ለመውጣት ቀለል ያለ አማራጭ የነበረ በመሆኑ ማንነቱን ከሌላ ሃይማኖት ጋር
ካስተሳሰረው መንግሥት ሥር ፖለቲካዊ ተሳትፎ የማድረጉን አስፈልጎት አስወግዶታል።
በተመሳሳይ ሁኔታ
አርብቶ አደርነት ከመንግሥት የሥልጣን ማዕከል ርቆ የሚሠራ ሥራ በመሆኑ መንግሥት ቀጥተኛ ቁጥጥር ሊያደርግ
የሚችልበት ዕድል አልነበረም። በልዋጩ ትናንሽ አካባቢያዊ መሪዎችን ነጻነት በመሥጠት በፍቃደኝነት እንዲገብሩ ማድረግ
ብቸኛው አማራጭ ነበር። ይህ በወረሩት ቦታ ላይ ሠፍሮ በቀጥታ የተፈጥሮ ሐብቱ ለማዕከላዊ መንግሥት እንዲውል
ይደረግ የነበረበት አሠራር የሚፈጥራቸው ግጭቶችና ሰበቃዎች እንዳይፈጠሩ ማድረጉ አይቀሬ ነው። በጥቅሉ በዘውዳዊው
አገዛዝ ውስጥ ሙስሊም ልሂቃን በፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ግፊት አላደረጉም፤ ቢያደርጉም የሚያስተናግድ ሁኔታ (ከባቢ)
አልነበረም። በጊዜ ሂደትም ውጤቱ ነጋዴዎች የትምህርትን አስፈላጊነት እንዳያውቁ፣ አርብቶ አደሮች ደግሞ ለመማር
ዕድሉን እንዳያገኙ ሆነ።
ሐ/ በሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻ አጋማሽ እያደገ የመጣ ጭቆና እና አመቺ ውጫዊ
ሁኔታዎች ቢኖሩም የተራማጅ (progressive) እና ብሔርተኛ (nationalist) የፖለቲካ ዝንባሌ አገሪቱን
በመቆጣጠሩ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ አደረጃጀት (ንቅናቄ) መግቢያ አላገኘም። በግራ ዘመሞች ትግል ሊሳካ የበቃው
የሃይማኖትና መንግሥት መለያየትም የሙስሊሞችን ዋነኛ የቅሬታ ምንጭ አስወገደው። የሙስሊሙን ጥያቄ እውቅና በመስጠትና
በመደገፍ ተራማጁ የፖለቲካ ዝንባሌ ለብቻው የቆመ ሃይማኖታዊ ትግል እንዳያስፈልግ አደረገ። በተመሣሣይ ሁኔታ
ብሔርተኛ (nationalist) እንቅስቃሴዎች (የኦሮሞ፣ ኤርትራና ትግራይ) በሚያደርጉት ትግል የተለያዩ ሃይማኖቶች
ተከታይ አባላት ያሏቸው በመሆኑ የሃይማኖት መቻቻልና የባህል ተመሳስሎሽን በመስበክ ሃይማኖትና መንግሥት
እንዳይገናኙ ጥረት አድርገዋል። በሌላ አነጋገር ብሔርተኛ ንቅናቄዎች ለሙስሊሞች ሃይማኖታዊ ማንነት፣ ቅሬታና ስሜት
እውቅና በመስጠት መሉ በሙሉ ዓላማዊ በሆነው ትግል ውስጥ ግባቸውን እንዲቀርፁ ዕድል ሰጧቸው።
በጥቅሉ
የእስልምና ንቅናቄ ወደ ብሄርተኛ ንቅናቄ እንዲለወጥ መደረጉና የሃይማኖት ጭቆና በተራማጅነት እና ብሔርተኝነት
በመተካቱ የሙስሊሞች የትግል አሰላለፍ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ እንዳይሆን አድርጎታል።
1. 2. የሙስሊሙማኅበረሰብመለወጥ
ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት የተከሰቱት ማኅበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ቀስ በቀስ ለውጠውታል። የተወሰኑትን እንዳስሳቸው፡-
ሀ/ ንግድ ዛሬ የሙስሊሞች ብቻ ሞያ መሆኑ ቀርቷል። ከ 1967ቱ አዲስ የመሬት ድልድል በኋላ የቀድሞ ባላባቶች
እና መሳፍንቶች ወደ ንግድ በመግባታቸው ዘርፉን ተፎካካሪ ያለበት ሙያ አድርጎታል። ከደርግ ውድቀት መልስ ትጥቅ
የፈቱ የትግራይ ወታደሮችም የጅማሮ ካፒታል ተወጥቷቸው ወደ ንግዱ መቀላቀላቸው ለገበያው ተጨማሪ ጫና ሆኗል። በፓርቲ
የሚተዳደሩ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች መቋቋማቸውና አዋጭ የሚባሉትን ዘርፎች መቆጣጠራቸውም ሙስሊሙ ተሠማርቶባቸው
በነበሩት እንደቡና ንግድ ያሉ ዘርፎች ትናንሽ እና መካከለኛ ነጋዴዎች ላይ ጫና ፈጥሯል። እናም ንግድ ለአዲሱ
ሙስሊም ትውልድ አዋጭ ሥራ ሊሆን አልቻለም።
የአየር ንብረት ለውጥ በበኩሉ አርብቶ አደርነትን እጅግ አስቸጋሪ
ሞያ አድርጎታል። ተደጋጋሚ ድርቅ ከብቶችን እየጨረሰ በመሆኑ የጥንት ሞያቸውን እንዲተዉት እያደረገ ነው። እናም
አዲሱ ሙስሊም ትውልድ የአባቶቹን አርብቶ አደርነት ሞያ እየተወ የተሻለ ሥራና ዕድገት እንዲፈልግ አስገዳጅ
ሆኖበታል። በአገሪቱ ከሚገኙ የደመወዝ አስገኚ ሥራዎች 80 በመቶው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመሆናቸው የመንግሥት
ሥራ ተቀጣሪነት የተሻለው አማራጭ ሆኗል። ለዘመናዊው የመንግሥት ሥራ ደግሞ ትምህርት የግድ በመሆኑ ሙስሊም ወላጆች
ልጆቻቸውን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ወደ ትምህርት ቤት መላክ ጀመሩ። እነዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ደግሞ ሲመረቁ
መንግሥት ሥራ ላይ እንዲመድባቸው መጠየቃቸውና መጠበቃቸው አልቀረም። መንግሥት በበኩሉ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ
አለመቻሉ አሁን የምናየውን የሙስሊም ማኅበረሰብ የመብት ንቅናቄ (activism) ፈጥሯል።
ለ/ ባለፉት ጥቂት
አሥርት ዓመታት ልክ እንደተቀረው የዓለም ክፍል ሁሉ በኢትዮጵያም እስላማዊ መነቃቃት ተከስቷል። መነቃቃት ሲባል
የመንፈሳዊነት ፍላጎት መጨመርና የሃይማኖታዊ አስተምህሮቶች መጎልበት ለማለት ነው። ይህ መነቃቃት በተለይ ደግሞ
ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በጣም አድጎ ታይቷል። ሃይማኖትን የማጥላላት ዘመቻ ከፍቶ የነበረው ደርግ ማኅበረሰቡን
በጥብቅ ማዕከላዊ ቁጥጥር ሸብቦ ለአሥራ ሰባት ዓመታት በማቆየቱ በ 1983 የተከሰተው የከፊል ዴሞክራሲ እና
ያልተማከለ (decentralized) አመራር ለውጥ የሃይማኖት አስፈልጎትም ሆነ አቅርቦት እንዲጨምር አድርጓል።
የፕሬስ ነጻነት በተነፃፃሪ መልኩ እፎይታ በማስገኘቱም ሃይማኖት ነክ ሥራዎች እንዲተረጎሙ፣ እንዲታተሙና እንዲከፋፈሉ
በር ከፍቷል። የመሃይምነት መጠን መቀነስ በበኩሉ ሰዎች ለገበያ የቀረቡትን መጽሐፍት እንዲያነቡ አድርጓቸዋል።
የትራንስፖርት መሠረተ ልማት መዳበር፣ የቴሌ ኮሚውኒኬሽን አገልግሎት መሻሻል፣ እየጨመረ የመጣው ከገጠር ወደ ከተማ
ፍልሰት፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መርከስ እና በቅርቡ ደግሞ የማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ሚዲያዎች መጎልበት
የመረጃ ልውውጡን በእጅጉ ጨምሮታል። እኒህ ሁሉ ተዳምረው ሰፊ ሃይማኖታዊ መነቃቃትን ፈጥረዋል።
ሃይማኖታዊ
መነቃቃት በባሕሪው በባህላዊያን (traditionalists) እና በዘመናዊያን (modernists) መካከል ፍትጊያ
መፍጠሩ አይቀሬ እንደመሆኑ መጠን አማኞች በተፎካካሪ ቡድኖች ተቦዳድነው ክርክር መፍጠራቸው አልቀረም። ምንም እንኳን
ድብቅ ፍጥጫዎች (isolated confrontations) መጀመሪያ አካባቢ ይታዩ የነበረ ቢሆንም በአስገራሚ ሁኔታ
በጊዜ ሂደት የባህላዊያኑም ሆነ ዘመናውያኑ ንቃተ ሕሊና ማደግና የተሻሉ የመዳረሻ ሥልቶችን መጠቀም መነቃቃቱ
ሰላማዊ ግስጋሴ እንዲኖረው አድርጓል።
ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ለውጥን እና የሃይማኖት መነቃቃትን በተመሳሳይና
በአንድ ወቅት ማስተናገዱ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ንቃት ከፍ እንዲል በማድረጉ ምክንያት አንዳንድ ወገኖች ሁለቱ
የተለያዩና ለየብቻ የተከሰቱ ለውጦች አንድ ክስተት መስለው እንዲታዩዋቸው ሆኗል። በዚህም ‹‹አክራሪነት›› በሚል
ፈርጀውታል።
1. 3. ባለበትየሚረግጠውመንግሥት
በሙስሊሙ ማኅበረሰብ መካከል ከላይ የጠቀስናቸው ለውጦች ተካሄደው ሳለ መንግሥት ለውጡን ለማስተናገድ ያደረገው መዋቅራዊ ማስተካከያ አለመኖሩ ሌላው ችግር ነው።
ሀ/ ማዕከላዊው አሥተዳደር በፌዴራሊዝም በመተካቱ ዱሮ ተገፍተው የነበሩ ቡድኖች ልሂቃን (elites) ከገዢው
ፓርቲ ጋር በሚኖር ትሥሥር ሥር ከአገሪቱ ሐብት ተካፋይ እንዲሆኑና ሕዝባቸውንም እንዲያስተዳድሩ አድርጓል። ነገር
ግን ያገኙት የይስሙላ ሥልጣን ከክልላዊ፣ ዞናዊና አውራጃዊ ደረጃ ያለፈ ባለመሆኑ ወደ ላይ በመሰላሉ የመውጣት ዕድል
(upward mobility) አላገኙም። በሚኒስትር ደረጃ ጥቂት ሙስሊሞች ከመኖራቸው ባለፈ ማዕከላዊው አሥተዳደር
እና ፖለቲካዊ መዋቅር ውስጥ ሙስሊሞች የሉም። በመሆኑም የታችኛው መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ የሙስሊሞች ብቅ ማለት
የፈጠራቸው ማኅበረሰባዊ ለውጦች ቢኖሩም የላይኛው ማዕከላዊ መዋቅር ከነዚህ ለውጦች የተጋረደ ነው። ለውጡን
ለማስተናገድ ያመቻቸው ነገርም የለም።
ለ/ የአገራዊ ማንነት (identity) ቅርፅ አሁንም አለመቀየሩ
ሙስሊሙ በገዛ አገሩ የባዕድነት ስሜት እንዲሰማው ካደረጉ እንቅፋቶች አንዱ ነው። የይስሙላ እኩልነት እና የተሻለ
ሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦችን የማስተናገድ ሁኔታ ከመንግሥት በኩል ቢኖርም የኢትዮጵያ ማንነት፣ ተምሳሌትና ይዘቱ ጭምር
(symbol and compostion) አሁንም ከክርስትና ጋር የተዛመደ ነው። ለማሳያነት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን
እና ኤምባሲዎችን መጎብኘት ብቻውን በቂ ነው። ይህ ዓይነቱ ውሱን አገራዊ ማንነት ደግሞ አዲሱን ሙስሊም ትውልድ
የማስገለል ሚና ይጫወታል።
እነዚህ የተማረ፣ ጉጉ እና ማንነቱን የቀረፀ ትውልድ ፍሬ የሆኑ ወጣቶች ደግሞ
ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች የተገፉ እንዲመስላቸው ያደርጋሉ። ‹‹ተገፋን›› ብለው ገለል ይላሉ። ነገር ግን እንደ
አባቶቻቸው ኑሯቸውን የሚገነቡበት ሌላ ሞያ ስለሌላቸው ተመልሰው በሩን መቆርቆርና ተጨባጩን ለመለወጥ መታገል
ይጀምራሉ። አሁን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።
1. 4. አባባሽየመንግሥትፖሊሲዎች
ሀ/ አሁን
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሥልጣኑን ሲቆጣጠር ዋነኛ ሥጋቱ የነበረው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ነበር። የኦሮሞ
ብሔርተኝነት ደግሞ ከጅማሮው አንሥቶ የሃይማኖት መሪዎችን የማካተት፣ የማበረታታትና ከነሱ ድጋፍ የማግኘት ሁኔታ
ነበረው፤ በተለይ ደግሞ ከሙስሊም እና ፕሮቴስታንት የሃይማኖት መሪዎች በኩል። አገዛዙ ይህንን የሙስሊሞች ድጋፍ
ከእንጭጩ ለማክሰም በባሕላውያኑ እና በዘመናውያኑ ሙስሊሞች መካከል ከዱሮም የነበረውን ልዩነት በሚገባ ተጠቅሞበታል።
ይህ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የተራገበው ልዩነት አሁን ለተፈጠረው ንቅናቄ አንዱ ምክንያት ነው።
ለ/
መንግሥት ልክ እንደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ሁሉ እስላማዊ ተቋማትንም በራሱ ቁጥጥር ሥር በማዋል ለራሱ ፖለቲካዊ
ጥቅም አውሏቸዋል። በውጤቱም አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች እንደ መንግሥት አስፈጻሚ ባሕሪ ሲላበሱ፣ ተቋማቸውም ልክ
እንደ መንግሥት ተቀፅላ መዋቅር መሆን ጀመረ። ይሄኔ አማኞች በተቋማቱ ላይ ያላቸው እምነት በመሳሳቱ ኢ-መደበኛ
አመራርና ድርጅቶች ብቅ ማለት ጀመሩ።
ሐ/ ባለፉት አሥር ዓመታት የመንግሥት አሰላለፍ ወደ ቀን ዘመምነት
ተቀይሯል። በዓም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ለውጦች የፈጠሩትን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ለሥልጣኑ አስጊ የሆኑ ውስጣዊ
ክስተቶችን ተከትሎም ቀደም ሲል ማርክሳዊ የነበረው መንግሥት የቀኝ ዘመም ፖለቲካ አሰላለፍን መርጧል።
በሂደት
አላስፈላጊ ክልከላዎችን (ትምህርት ቤት ውስጥ ሂጃብና ሶላትን መከልከልን የመሰለ) በማስተዋወቅ፣ ረዘም ያለ ፂም
ያላቸውን ወጣቶች በማዋከብና በአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ቅያሜ የሚፈጥሩ ንግሮችን በማስነገር ስትራቴጂውን
ገፋበት። ይህ ደግሞ በተራው የድሮው ጭቆና ቁስል እንዲያመረቅዝ በማድረጉ ከፍተኛ መነቃቃት በሙስሊሙ ዘንድ ተፈጠረ።
መንግሥት ሙስሊም የመብት ንቅናቄ አራማጆችን ‹‹የኅቡእ ታጣቂ ቡድን አባል ናቸው›› በሚል ማዋከቡና ከውጭ
እንዲመጣ የተደረገው የሃይማኖት አንጃ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥመው ‹‹አለም አቀፍ አሸባሪዎች የመደቡት በጀት ሥራ
ነው›› በሚል አጀንዳ ሊያስቀይር መሞከሩ ጥሩ አይደለም፤ ለዘብተኞች እንዲዳከሙና ጠንከር ያለ አቋም ያላቸው ደግሞ
ኃይል እንዲያገኙ ያደርጋልና።
በተመሣሣይ ሁኔታ የቀኝ ዘመም ፖለቲካዊ አሰላለፍ በ 1997 ምርጫ ወቅት ዳግም
በማንሠራራቱ ገዢው ፓርቲ እንደአፀፋ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን (Ethiopian Nationalism) ከፍ ባለ
ድምጽ መዘመሩ እንደሚያዋጣው በመገመት ተያይዞታል። በሚሌኒየሙ ጅማሮ የተጀመረው የ‹‹ኅዳሴ›› ፕሮፓጋንዳ ወደ አባይ
ግድብና ተያያዥ ሥጋቶቹ ተሸጋግሯል። በመሆኑም አዲሲቷ ኢትዮጵያን የመገንባቱ መፈክር ተቀይሮ ‹‹የዱሮ
ታላቅነታችንን መመለስ›› በሚል ተተክቷል። ያለፈው ታሪካችን ደግሞ ለሙስሊሙ ማኅበረሰብና ለሌሎች ጭቁኖች ሁሉ
የነበረው ትርጉም የማያስደስት በመሆኑ አሁን መንግሥት እያስተላለፈ ያለው መልዕክት ከዱሮው ያልተለየ ይሆንባቸዋል።
እናም ይህ ሕዝበ ሙስሊሙን እንደ ውጭ አካል የማየትና ጥያቄውን የመኮነን አቅጣጫ የመገለል ስሜቱን እንደ አዲስ
በመቀስቀስ ንቅናቄ ፈጥሯል።
የፖለቲካ አመራርክፍተትና ምሁራዊ ምሪት አልባነት
የሙስሊሙም ሆነ
ክርስትያኑ ማኅበረሰብ ሃይማኖታዊ መነቃቃት እየጦዘ ያለው በፖለቲካ መሪዎችና በምሁራን ዘንድ ጠንካራ ውይይት
(discourse) በጉዳዩ ዙሪያ በሌለበት መሆኑ ችግሩን አባብሶታል። ሃይማኖት ፖለቲካውን ሠርጎ እንዳይገባ
(politicization of religion) በሚደረገው ጥንቃቄም የፖለቲካ መሪዎች ወደ ችላ ባይነት ወይም
ለሃይማኖታዊ ውይይት ስሱ (sensitive) ወደ መሆን አዘነበሉ። በውጤቱም ፖለቲከኞችና ምሁራን በሃይማኖት ዙሪያ፣
በተለይ ደግሞ እስልምናን በተመለከተ ጥናት ማጥናትም ሆነ አስተያየት መስጠትን እንደ አደገኛ ጨዋታ ቆጠሩት። ይህ
ፍርሃት ከመስከረም አንዱ ጥቃት በኋላም ጨምሮ ታይቷል። ሙስሊም ፖለቲከኞችም አጀንዳውን ስለሚፈሩት ከማኅበረሰባቸው
እንዲነጠሉ ሆነዋል። ጥቂት ሙስሊም ምሁራን ናቸው ደፍረው ስለ እስልምና የሚከታተሉት፣ የሚያጠኑትና
በማኅበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጽፉት።
አንዳንዶች በኢሕአዴግ ከፍተኛ የሥልጣን መዋቅሮች
ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ሙስሊም ባለሥልጣናትን በማየት ተሳትፎው ጥሩ እንደሆነ ሊሞግቱ ይሞክራሉ። ነገር ግን እኒህን
ባልሥልጣናት ሙስሊሙ እንደ ሙስሊም መሪዎች አልተቀበላቸውም። ምክንያቱም ከማኅበረሰባቸው ጋር ያላቸው ትስስር የሳሳ፣
የማኅበረሰባቸውን አመለካከትም ሆነ ፍላጎት የማይረዱ፣ ግድ የማይሰጣቸውም ጭምር ስለሆኑ ነው። እንዲህ ስል
ባለሥልጣናቱ ሃይማኖትን የወገን አሠራር ይከተሉ ማለቴ አይደለም። እኔ እያልኩ ያለሁት ማኅበረሰባቸው ውስጥ ሥር
የተከሉ ቢሆኑ ኖሮ ለመንግሥት ትክክለኛ መረጃ ባደረሱና የመንግሥትንም ፖሊሲዎች የበለጠ ወደ ሕዝቡ ማስረፅ በቻሉ
ነበር ነው።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድም ቢሆን ተመሳሳይ ነገር ነው ያለው። ሁሉንም ሃይማኖቶች ባማከለ መልኩ
የሚንቀሳቀሱት ብሔርተኞች (nationalists) ሲቀሩ ሌሎቹ በሙሉ ያላቸው የሙስሊም ተሳትፎ ወደ ዜሮ የተጠጋ
ነው። በቀደመው ጊዜ ውስጣዊ ትስስራቸውን ጠብቆ ለማቆየት፣ ከመስከረም አንዱ ጥቃት በኋላ ደግሞ በሽብርተኝነት
ላለመፈረጅ ሲሉ እስልምናን መሸሽ ይመርጣሉ። ይህ በአመራሮቻቸው መካከል የሙስሊሞች መታጣት የሙስሊሙን ማኅበረሰብ
ሮሮ፣ ፍላጎት፣ አመለካከትና ስሜት እንዳያውቁ አድርጓቸዋል። ትርክታቸውም የሙስሊሙን ድጋፍ እና ተሳትፎ የሚገፋ
እንጂ የሚያቀርብ አይደለም።
የፖለቲካ ልሂቃን ድርጅቶቻቸው የአንዱን የሃይማኖት ማኅበረሰብ ብሶት፣ ፍላጎት፣
አመለካከት ካላወቁ ደግሞ ቀውስ ሲፈጠር ሊያረጋጋ የሚችል ፖሊሲ መቅረፅ ይሳናቸዋል። ይሄኔ ክፍተቱን ለመሙላት ብቅ
የሚሉት እንደ ፖለቲካዊም ሃይማኖታዊም መሪ ሆነው የሚያገለግሉ የሃይማኖት መብት ንቅናቄ አራማጆች ናቸው። ይህ ደግሞ
ብዝኀ ሃይማኖት ባለበት አገር ውስጥ ዓለማዊ ፖለቲካ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅእኖ ቀላል አይደለም::
ይኸው አመክንዮ ለልሂቃኑ መደብም ይሠራል። እስካሁን በአገራችን ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ የተደረገው ጥናት እጅግ
የሳሳ ነው። ባለፉት መቶ አመታት ውስጥ በጉዳዩ ላይ የተጻፉት ደህና የሚባሉ መጽሐፍት ሁለት ብቻ መሆናቸው
ያስገርማል። ጄ.ኤስ ትሪሚንግሃም “Islam in Ethiopia” የሚለውን መጽሐፉን ካሳተመ ከግማሽ ምዕተ ዓመት
በኋላ ነው የፕሮፌሰር ሑሴን አሕመድ “Islam in the 19th Century Wollo” የተከተለው። ከዚህ ውጭ
ያሉት ሥራዎች ትናንሽ መጽሐፍቶች፣ መጣጥፎችና ምዕራፎች ናቸው። ይህ እንግዲህ ከላይ እንደጠቀስኩት አገሪቱ ማምረት
የቻለችው ሙስሊም ምሁራን እጅግ ጥቂት በመሆናቸው ነው። እኒህም ጥቂቶቹ ቢሆኑ በ 2009 ካረፈው ፕሮፌሰር ሑሴን
አሕመድ ውጭ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ አኗኗር ዙሪያ ጥሩ የጽሑፍ ሥራ ያበረከቱ አይደሉም።
ምንም እንኳ የትምህርት
ዕድሉ እየሰፋ የሄደ ቢሆንም እየተበራከቱ ያሉት ምሁራን ወይ ሥነ-መለኮታዊውን ክፍል ብቻ መዳሰስ፣ አልያም
ከነጭራሹ ርእሱን መተው መርጠዋል። በመሆኑም ምሁራዊ ምልከታ በሌለበት ሁኔታ እውቀት እየተመረተ እና እየተሠራጨ
ያለው ስሜት በተጫናቸው የንቅናቄ አራማጆች ነው። ከአስተማሪ ይልቅ አነሳሽ የሆኑ ጽሑፎች እየተበተኑ ያሉትም ለዚህ
ነው። ሙስሊምም ሆነ ሙስሊም ያልሆኑ ምሁራን ጥልቅ ጥናቶችን በመሥራት ማኅበረሰቡን ማወያየትና ማሳተፍ ያለባቸውም
ለዚህ ነው። ችላ ባይነቱ ከቀጠለ ግን አስከፊ ፍፃሜ ሊይዝ ይችላል።
ያልተገራጣልቃገብነት
የሙስሊሙን
ኅብረተሰብ ማኅበራዊ ለውጥ ማስተናገድ ያልቻለው፣ መቻቻልን ያጠናክሩ የነበሩ ዕድሜ ጠገብ እስላማዊ ተቋማትን ቅርብ
አሳቢ (short-sighted) በሆነ እርምጃ ያዳከመው፣ ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ለማስቀየም የበቁ አጓጉል ሃይማኖታዊ
ክልከላዎችን የተገበረው የኢሕአዴግ መንግሥት አሁን ደግሞ ‹‹እስልምናን ለማለዘብ›› በሚል ምክንያት አደገኛ
ስትራቴጂ እየተከተለ ነው። እርግጥ ለዘብተኛነት (ሚዛናዊነት) ለአንድ አገር አስፈላጊ ግብዓት ነው። ነገር ግን
ከውስጥ ከሃይማኖቱ የሚመነጭ እንጂ ከውጭ መጥቶ የሚጫን አይደለም። መንግሥት ግን ከውጭ አገር አንድን የሃይማኖት
አንጃ በማስመጣት ‹‹ለኢማሞች ስለለዘብተኝነት ትምህርት እየሰጠሁ ነው›› እያለ ነው።
ይህ ስትራቴጂ በውስጡ
ብዙ ችግሮች አሉት። በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት አንድን የሃይማኖት አንጃ መርጦ የማምጣትም ሆነ የመጫን መብት
የለውም። ይህ ግልፅ ባለ ሁኔታ ከመንግሥትና ሃይማኖት መለያየት መርህ ጋር ክፉኛ የሚጣረስ ነው። በሁለተኛ ደረጃ
ደግሞ ከላይ ከአመራር ወደታች ወደ ሕዝቡ ሃይማኖትን አውርዶ ለማጥመቅ የሚደረግ ሙከራ ሊሳካ የማይችል ስትራቴጂ
ነው። የትኛውም ማኅበረሰብ ቢሆን ከውጭ የሚመጣ ተፅእኖን በጥሩ ዐይን ሊያይ አይችልም። ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ ሲሆን
ደግሞ ጥርጣሬው የበለጠ ነው የሚጨምረው፤ ራሱን በብርቱ ለመከላከል ይሞክራልና። ስለዚህ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ
መንግሥት እየወሰደ ያለውን አንድን አንጃ የመደገፍ እርምጃ ‹‹በግድ ሃይማኖትን እንደ ማስቀየር›› አድርጎ ማየቱ
አስገራሚ አይደለም። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ መንግሥት ስትራቴጂውን የመሠረተው በተሳሳተ ሐሳብ ላይ መሆኑ ሌላ ችግር
ነው። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያንን ከፍተኛ አመራር መቀየርና መሾም ስለቻለ እስልምና ጉዳዮችም ላይ ተመሳሳይ ነገር
ማድረግ እንደሚቻል አድርጎ አስቧል።
ክርስትና (በተለይ ደግሞ ኦርቶዶክስና ካቶሊክ) በምእመናን ላይ ጥብቅ
ቁጥጥር ያለውና ግልፅ የሥልጣን ተዋረድ መዋቅር የሚከተል የተማከለ የሃይማኖት አመራር ያላቸው ቢሆንም በእስልምናው
ግን ከዚህ በተለየ መልኩ እያንዳንዱ መስጊድ እና የሃይማኖት መሪ የየራሱን ሥልጣን በነጻነት የሚጠቀምበት ሁኔታ ነው
ያለው። መስጊዶችን የሚገነባው የየአካባቢው ማኅበረሰብ እንደመሆኑ መጠን ኢማሞቹም ብዙ ጊዜ ያለደመወዝ
የሚያገለግሉት እዚያው ከማኅበረሰባቸው መሐል ከተመረጡ በኋላ ነው። ሰባኪያኑ (የመስጊዱ ኢማም ሊሆኑም ላይሆኑም
ይችላሉ) ምእመናንን የሚስቡት በግላዊ እውቅና ሲሆን ማዕከላቶቻቸውም በዚያው ማኅበረሰብ ድጋፍ የሚቆሙ ናቸው።
በመስጊዶች መካከል የተዘረጋ ኔትወርክ ባለመኖሩም አንድ ሰባኪ (ዳዒ) የሚያስተምረውን፣ አንድ ኢማም የሚሰብከውን
እና መስጊዱ እንዴት መተዳደር እንደለበት የሚቆጣጠር አካል ከላይም ከታችም የለም። ይህ የተማከለ አመራር እና
አገልግሎት ለመስጠት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባዔ ከተቋቋመ በኋላም እንኳ ሊቀየር ያልቻለ የኢትዮጵያ
እስልምና ባሕሪ ነው። ምንም እንኳ ዘመናዊው የመነቃቃት እንቅስቃሴ መደበኛ ማሠልጠኛ ማዕከላትንና ጥራቱን የጠበቀ
ይዘትና የአማማር ዘይቤ ያስተዋወቀ ቢሆንም የተማከለና የተናበበ የአመራር ማዕከል ማቋቋም አልተሳካለትም። ምክንያቱም
በየቦታው ያሉት መስጊዶች የየራሳቸውን ነጻነት ለማስጠበቅ ስለማይሰንፉ ነው።
በጥቅሉ የኢትዮጵያ እስላማዊ
ተቋማት አደረጃጀት እጅግ ያልተማከለና ሁሉም በየራሳቸው የሚቆሙበት ስለሆነ ከላይኛው ተዋረድ የሚመጣ ለውጥ መሬት
ሊያገኝ አይችልም። ለዚህም ነው ባህላዊውና ዘመናዊው ንቅናቄ ያደረጓቸው ፍትጊያዎች ከማዕከላዊው ተቋም ይልቅ
መስጊዶችን በመቆጣጠር ላይ አትኩረው የቆዩት። መንግሥት ስትራቴጂውን ሲነድፍ ይንን መሠረታዊ ባሕሪ ክፉኛ በመሳቱ
ልፋቱ ሁሉ መና እየቀረበት ይገኛል።
አሳስቶ ከማቅረብ ወደ ማመቻመች (From Mispresentation to Accomodation)
እስልምናና ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በአገራችን ኢትዮጵያ ወሳኝ በሆኑ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና
መንፈሳዊ ለውጦች ውስጥ እያለፈ ነው። ይህን መሰሉ ለውጥ ደግሞ ማኅበራዊ ውጥረት (stress) መፍጠሩ አይቀሬ
ነው። ይህንን ከዓለም አቀፉ አየር ጋር አዋድደን ስናገናዝበው ውጥረቱ አጉል ትኩረትና የመረበሽ ስሜትን በውጫዊም
ሆነ ውስጣዊ ባለድርሻ አካላት ዘንድ ሊፈጥር ይችላል፤ መፍጠሩም የሚጠበቅ ነው። ነገር ግን ለችግሩ አጫጭርና ጊዜያዊ
የመፍትሄ እርምጃዎችን በችኮላ ከመውሰድ ይልቅ ሩቅ አሳቢ፣ አዎንታዊና አስተናጋጅ (አመቻማች) መሆኑ አዛላቂ ሆኖ
ይገኛል። ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገው ስለኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ እውነታ
ትክክለኛና የጠለቀ እውቀት መጨበጥ ነው።
የመንግሥት ባልሥልጣት እየተፈጠረ ያለውን የሙስሊሞች የንቅናቄ ስሜት
አንሻፈው ማቅረባቸውን ማቆም ይገባቸዋል። በዚህ መጣጥፌ ውስጥ ለማሳየት እንደሞከርኩት እስላማዊ መነቃቃቱ
የዓለማቀፍ ክስተቶች ተፅእኖ ያረፈበትና የክስተቶቹ አንድ አካል ጭምር ቢሆንም ተዋናዮቹ፣ መግፍዔው (motive)
እና መንስዔዎቹ አገር በቀል ናቸው። በቅርቡ በዶክተር ቴሪ (ተርጂ) ኦስቴቦ የተሠራው “Religious Change
among Oromo Muslims in Bale” የተሰኘ ጥናት እንደሚያሳየው አሥርት ዓመታትን የፈጀው ዘመናዊው
የዳግም መነሳሳት (revivalism) ንቅናቄ የተነሣው፣ የተቀረፀውም ሆነ በቁጥጥር ሥር የዋለው በአገር በቀል
ተጨባጮች ነው። ይህ የትኛውም ሚዛናዊና ከወገንተኝነት የፀዳ አእምሮ ያለማመንታት የሚቀበለው እውነታ ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ ምንም እንኳን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በመንፈሳዊ ጉዳዮች ከሌሎች አገራት ሙስሊሞች ጋር አንድነት
እና አጋርነት ቢኖራቸውም ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ብሶቶቻቸውን ያቅጣጩት ወደ ኢትዮጵያው መንግሥት ነው። እኒህን
እውነታዎች ለጊዜያዊ ጥቅም ሲባል አንሻፍፎ ማቅረብ ለውጡን ለማስተናገድ የማይመች ከባቢ ከመፍጠሩም ሌላ ውጥረቱንም
የበለጠ ያጎነዋል። በቀደሙት ዘመናት የሙስሊሞች ጥያቄ ሃይማኖታዊ ነጻነትና እኩልነትን በመጠየቅ የተወሰነ ነበር።
ዛሬ ግን አዲሱ ሙስሊም ትውልድ መካተትን፣ ውክልናን እና ሙሉ ተሳትፎን ነው እየጠየቀ ያለው፤ የመንግሥት ጣልቃ
ገብነት ላይ ከተነሣው አገራዊ ተቃውሞ ሌላ ማለት ነው።
በጥቅሉ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ፍላጎቶቻቸው፣
ዕይታዎቻቸው እና ምኞቶቻቸው ሁሉ በፖሊሲ ቀረፃ፣ በአገራዊ ትርክትም ሆነ ምስል ቀረፃ ውስጥ እንዲካተቱላቸው
እየፈለጉም፣ እየታገሉም ነው። እኒህ ደግሞ የሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ጥያቄዎች አይደሉም፤ በሰላማዊ ተቃውሞ ላይ
የተመሠረተ ዓለማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እንጂ። ይህ በአገሪቱ ድንበሮች ሥር ተወስኖ ያለ የመብት እንቅስቃሴ
ጥያቄውን ያቀረበው ለመንግሥት እንደመሆኑ መጠን መፍትሄውንም የሚጠብቀው ከዚያው ነው።
የሥርዓቱ ከፍተኛ
ባለሥልጣናት እያሰሙት ያለው የሥጋት ጩኸት እና ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አካላት ጠጣር ገለጻ
እየጮኸ ቢሆንም ድሮም ሆነ ዛሬ የተለየ ኢስላማዊ የፖለቲካ ሰውነት እንዲኖር ሙስሊሞች የጠየቁበት ጊዜ የለም። መሰል
አቀራረብን የመረጡ ፖለቲካዊ ተቋማት እንኳ ከሙስሊሙ ኅብረተሰብ ክፉኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ከፊሎቹ አስተሳሰባቸውን
ለመለወጥ ሲገደዱ ከፊሎቹ ከስመዋል።
እስካሁን ድረስ ከልላዊ እና አገራዊ ታጣቂ ቡድኖች ተደጋጋሚ ጥሪ
ቢያደርጉለትም፣ መንግሥትም ተንኳሽ እርምጃዎችን ቢወስድበትም የሙስሊሞች ንቅናቄ የኃይል መጠቀምን ዝንባሌ አላሳየም።
ይህ ለኔ የሚያሳየኝ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ነጻነት፣ የሕግ የበላይነት እና እኩልነት ከሕግነት ባለፈ ያለ
ሃይማኖት ልዩነት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እውን የሚሆኑበትን ተጨባጭ ከመፈለግ የመነጨ ትግል እንደሆነ ነው። እያደገ
ያለው የሙስሊሞች ንቅናቄ መድልዎን፣ ችላ ባይነትን እና ጣልቃ ገብነትን እየተቃወመ ያለ በመሆኑ የተበታተነው
ዴሞክራሲን የማስፈን ትግል አካል ነው ማለት ነው። የሥጋት ደውል የሚያሰሙትን ጥቂት ጩኸቶች ወደጎን በመግፋት
ጥያቄዎቹን ወደ መመለስ ማተኮሩ ኢትዮጵያን ወደ መረጋጋት እና አሳታፊ ልማት የሚያሻግር እጅግ አስፈላጊ እርምጃ
ነው።
(አቶ ጃዋር ሙሐመድ በእውቁ የአሜሪካ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪ ናቸው። በአገር አቀፋዊ እና
ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ ክስተቶች ዙሪያ ጥልቅ ፖለቲካዊ ትንታኔ በመስጠት ይታወቃሉ። ከላይ የቀረበው ጽሑፋቸውም
ወቅታዊ የሆነውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳይ አስመልክቶ ያቀረቡት ነው።
ለጽሑፋቸው ማጠናከሪያነት አሥር ያህል መጽሐፍቶችንና የጥናት ወረቀቶችን በዋቢነት ጠቅሰዋል።)
No comments:
Post a Comment