Wednesday, September 5, 2012

ኮሚቴዎቻችንና የኢማም አሕመድ ኢብን ሀንበል ጽናት


 እ.ኤ.አ. በ833 ዓ.ል. የሙስሊሙ ዓለም ኸሊፋ በመሆን ስልጣን የተቆጣጠረው አል-ማእሙን በዘመኑ ለፈተና የተፈጠረው የሙዕተዚላ አንጃ የሚያራምደውን ርዕዮት በሰፊው ህዝብ ላይ ለመጫን ተነሳ፡፡ በተለይ ቁርአን መኽሉቅ እንጂ ዘልዓለማዊ የአላህ ንግግር አይደለም የሚለውን የሙዕተዚላ አቋም የማይቀበለውን ማንኛውንም አሊም አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት ቆረጠ፡፡ ለዚህም ሚህና የሚባል የሽብርና የፈተና ሸንጎ አቋቋመ፡፡ በዚህ ሸንጎ ፊት ቀርቦ ቁርአን መኽሉቅ ነው የሚል ቃል ያልሰጠ አሊም በይፋ እንዲገረፍና ሀብቱ እንዲዘረፍ አወጀ፡፡
በዘመኑ የነበሩት ዑለማ በእጅጉ ተሰቃዩ፤ ተገረፉ፡፡ በርካቶችም የኸሊፋውን ቅጣት በመፍራት ቁርአን መኽሉቅ ነው አሉ፡፡ አንዳንዶችም ከሀገር ተሰደዱ፡፡ ታዲያ በዚያ የመከራ ዘመን ትክክለኛውን የአህሉ-ሱንና አቂዳ ለመጠበቅ ሰበብ ይሆን ዘንድ አላህ አንድ አስገራሚ ጀግና አስነሳ፡፡
ይህ ጀግና ታዋቂው አሊም ኢማም አህመድ ኢብን ሀንበል ነው (ረሒመሁላሁ ተዓላ)፡፡ ኢማም ኢብን ሀንበል በማእሙን የሚህና ፈተና ሳይሸበር ቁርአን ዘልዓለማዊ የአላህ ቃል ነው፤ የአላህ ቃል መኽሉቅ ነው የሚሉ ሰዎች ከኢስላም አፈንግጠዋል ብሎ ተናገረ፡፡ ኸሊፍ አል-ማእሙን ቃሉን እንዲያጥፍ ቢመክረው እንቢ አለ፡፡ በሹመት ቢያባብለውም በአቋሙ ጸና፡፡ በነገሩ የተናደደው አል-ማእሙን ኢማም ኢብን-ሀንበል በህዝብ ፊት እንዲገረፍ አዘዘ፡፡ ከዚያም ወደ እስር ቤት ወረወረው፡፡ አል-ማእሙን ከሞተ በኋላ የመሪነቱን ስልጣን የጨበጡት አል-ሙእተሲም እና አል-ወሢቅ የተባሉ ኸሊፋዎችም ኢብን ሀንበልን የሚችሉትን ያህል አሰቃዩት፡፡ ኢብን ሀንበል ግን ለቅጣት ሳይበገር በአቋሙ እንደጸና ቆየ፡፡
በ833 ዓ.ል. የተጀመረው የአል-ሚህና ፈተና ያበቃው በ848 ዓ.ል. አል-ሙተወኪል የተባለው ኸሊፋ ሲነሳ ነው፡፡ ይህኛው ኸሊፋ እውነተኛ ሙስሊም በመሆኑ የሚህናን ሸንጎ ወዲያውኑ ነው የበተነው፡፡ ኢብን ሀንበልንም ከነበረበት እስር ቤት በማውጣት በክብር አኖረው፡፡ ለግርፋትና ለስቃይ ያልተበገረው ኢብን ሀንበል በታሪክ ፊት ታላቅ ሰው መሆኑም ተመሰረከረለት፡፡ እነሆ በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዓ.ወ) የተለኮሰው የእምነትና የእውነት ብርሃን የኢብን ሀንበልን ጽናት መሸጋገሪያ በማድረግ ወደኛ ዘመንም ደረሰ፡፡
*****
ሀይማኖትን ልምረጥልህ ባዮች ህዝበ ሙስሊሙን መፈተናቸው ከጥንትም የነበረ ነገር ነው:: በኢብን ሀንበል ዘመን የነበረው ፈተና መልኩን እየለዋወጠ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተከስቷል፡፡ በቅርብ ዘመን እንኳ ታላቋ ሶቭየት ህብረትና ሌሎች የኮሚኒዝም ደቀመዛሙርት ተራውን ህዝብ ፈጣሪ የለም በሚል ርዕዮት ለማጥመቅ ከፍተኛ ዘመቻ አካሂደዋል፡፡ ይሁንና የኮሚኒስቶቹ ራዕይ አንዳች ፍሬ ሳያፈራ የሚመጻደቁበት ኮሚኒስታዊ ፍልስፍናቸው ከነርሱ ቀድሞ ተንኮታኮተ፡፡ እነ ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ለሀገራችን ኋላ ቀርነት መንስኤ የሆነው እስልምና ነው በሚል ተረት ተነሳስተው ኢስላማዊውን ፋና ከ50-100 ዓመታት በሚሆን ዘመን ከምድረ-ቱርክ ለማጥፋት የሚያስችል ሰይጣናዊ ማስተር ፕላን ቢነድፉም ውጤቱ የተገላቢጦሽ ነው የሆነው፡፡ ሌላም ብዙ ምሳሌ መደርደር ይቻላል፡፡
*****
በሐምሌ 2003 ደግሞ የፈተናው እጣ ለኛ ደረሰ፡፡ ህዝብን እንዲያገለግሉ የተሾሙ ዋልጌዎች ከህዝብም ከህገ መንግስትም በላይ ሆነው ህዝበ ሙስሊሙን መተንኮስ ጀመሩ፡፡ ወሃቢያ ስለሚባለው ምናባዊ አውሬ የተለያዩ ወጎችን ማሰራጨት ጀመሩ፡፡ ከጋዜጣ ላይ የቃረሙትን ቅንጭብጫቢ ወሬ በመንተራስ እስካሁን የቆያችሁበት እስልምና በጽንፈኝነትና በአክራሪነት የተሞላ ነው፡፡ ደግሞም ኋላቀርነት ስለሚበረታበት ለልማታችን አይበጅም፡፡ ስለዚህ ለዘመኑ እንዲስማማ ሆኖ የተዘጋጀ አሕባሽ የሚባል ዘመናዊ ርእዮት ከምድረ-ቤይሩት ስላስመጣንላችሁ መጅሊስ ወደ ሚባለው ቢሮ እየቀረባችሁ እንድትጠመቁ ይሁን፣ ያልተጠመቀ ሰው በጸረ-ልማትና በጽንፈኝነት እንደሚፈረጅ ከወዲሁ እናስጠነቅቃለን የሚል አዋጅ አስነገሩ፡፡
ህዝባችን ይህንን ህገ-ወጥ አዋጅ በህጋዊ መንገድ ለማስቀልበስ እንቅስቃሴ ጀመረ፡፡ በጥር ወር አጋማሽ ላይ ጥያቄዎቹን ለመንግስት የሚያቀርቡ ተወካዮቹን በመምረጥ ወደሚመለከተው አካል ሰደዳቸው፡፡ ውጤቱ ግን እምቢታ ሆነ፡፡ ሙስሊሙን ያለ ግብሩ አክራሪ፤ ጽንፈኛ እያሉ ማስፈራራትና መክሰስም ተጀመረ፡፡ በአርሲ ዞን አሳሳ ከተማ ንጹሃን ሰዎች በጥይት ተገደሉ፡፡ በመላው ሀገሪቱ በርካቶች ወደ ከርቸሌ ተወረወሩ፡፡ ይባስ ብሎ አዋጁን ያወጁት አካላት በሚሊዮኖች ፊርማ የተወከሉትን የሀገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ህዝቡ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን እንዲገለብጥ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርጋችኋል የሚል የፈጠራ ክስ በመደረት በዘመነ ቀይ ሽብር የቅጣት ትርኢት ማሳያ ዓይነተኛ ቦታ በሆነው ማዕከላዊ ምርመራ አጎሯቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውግዘት ከገጠመው የጸረ-ሽብር ህግ የተለያዩ አንቀጾች እየተመዘዙ የሞት ፍርድ ወይም የእድሜ ልክ እስራት አሊያም የ15 ዓመት እስራት ወዘተ እንዲፈረድባቸው የችሎት ሸንጎ ተጀመረ፡፡
*****
ወገኖቼ! ኢስላማዊው የህይወት ጎዳና ከተቀየሰበት ጊዜ አንስቶ ሙእሚን እንደተፈተነ ነው፡፡ ፈተናውን በብቃት ከተወጣ በዚህኛው ዓለምም ሆነ በመጪው ዓለም ከፍተኛ ሽልማት ይጠብቀዋል፡፡ ፈተናውን ከወደቀ ግን ለካስ በአላህ አምናለሁ፣ ለፈተና አልንበረከከክም የምትለው ሰውየ እንዲህ ሀሞተ ቢስ ኖረሀል! ተብሎ ከቃል አባዮች ተርታ ይመደባል፡፡ በወዲያኛው ዓለም ደግሞ ሌላ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ ስለዚህ በአሕባሽ ተመስሎ የተቀሰቀሰውን ፈተና ወድቀን ከቃል አባዮች ጋር እንዳንሰለፍ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ፈተናዎችን በብቃት ለመወጣት እንዲቻለንም በአርአያነታቸው የሚጠቀሱ አውራዎችን መከተል አለብን፡፡ አሁን ከገጠመን ፈተና አንጻር ተገቢ አርአያ ሊሆነን የሚችለው ደግሞ ጀግናው ምሁር ኢማም አሕመድ ኢብን ሀንበል ነው፡፡ ለአስራ አምስት ዓመታት ለግርፋትና ለጉንተላ ሳይበገር ትክክለኛው የአህሉ ሱንና አቂዳ ወደኛ እንዲተላለፍ ሰበብ ከሆነልን ኢብን ሀንበል ወዲያ አርአያ ሊሆነን የሚችለው ማነው? ማንም!
    *****
ኮሚቴዎቻችን ያለ ጥፋታቸው ታስረውብናል፡፡ ነገር ግን ፊት ከተነሱለት ዓላማም ሆነ ይከተሉት ከነበረው ርዕዮት ፍንክች አላሉም፡፡ በእስር ቤት ግርፋትና እመቃ ቢደርስባቸውም እስካሁን ድረስ ከጥንቱ መንገዳቸው አልተገለበጡም፡፡ በመሆኑም የኢማም አሕመድ ኢብን ሀንበል ጀግንነት በነርሱ ውስጥም እየታየ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢብን ሀንበል በመጨረሻው ላይ ጀግና የህዝብ ልጅ! ትክክለኛው የኢስላም ጠበቃ! ተብሎ በመቶ ሺሕ ህዝብ አቀባበል እንደተደረገለት ሁሉ የኛዎቹ ኮሚቴዎችም ፈተናዎቹን ሁሉ በብቃት በመወጣት የጀግኖች ጀግና ተብለው የሚወደሱበት ቀን ሩቅ አይደለም፡፡ ኢንሻ አላህ! በኢብን ሀንበል መንገድ ላይ በጽናት እንዲያቆማቸው ዱዓ እናድርግ፡፡ የኢብን ሀንበል መንፈስ በሁላችንም ውስጥ እንዲሰርጽ ጌታችንን እንለምነው፡፡
ድል የኢስላም ነው!

1 comment:

  1. የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
    እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.

    ReplyDelete