Sunday, May 27, 2012

መንግሥት በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ለቀረበው የመብት ጥያቄ የሰጠው ምላሽ አራምባና ቆቦ ነው


በሰይፈዲን አዳነ ዓለሙ (ሪርተር ጋዜጣ ግንቦት 19/2004)

አገራችን የተያያዘችውን የዕድገትና የልማት ጎዳና ቀጣይነት እንዲኖረው የማይፈልግ የኅብረተሰብ ክፍል አለ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ለዕድገትና ለልማት መስፈን ዋናው መሠረት ሰላም ነው፡፡ ሰላም ደግሞ ሊኖር የሚችለው በተጻፈ ብቻ ሳይሆን በሚተገበር ሕገ መንግሥት ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ መላው ሕዝብ ለሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ሳይሸራረፉ መተግበር የሚያደርጉት አዎንታዊ ሚና ለአገራችን ሰላም፣ ዕድገትና ልማት ወሳኝነት አላቸው፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ የሕዝቡን ፍላጎትና መብት በትክክል ማዳመጥና አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ግልጽና በይፋ የሚታየውን ሀቅ በመተው የማይመስልና በፍፁም ተቀባይነት የሌለውን ታፔላ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ላይ በመለጠፍ ዜጎችን ማስበርገግ፣ ብሎም አላስፈላጊ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ መዘጋጀት ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንን ለማለት የሚያስችሉ አንዳንድ ጉዳዮችን ቀጥሎ ማየት ይቻላል፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት ማንም ሰው የፈለገውን እምነት (ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ የሌሎችን መብት እስካልነካ ድረስ) የመከተል መብት ሊኖረው እንደሚገባ እየታወቀ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደአገራችን በይፋ የገባውን የአህባሽን የእስልምና ሴክት በግድ ተቀበሉ እየተባለ ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ማስገደድና ጫና መፍጠር የችግሮች ሁሉ ቁልፍ ችግር ነው፡፡ ለዚህም በመንግሥትና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (ያላንዳች ምርጫ ሙሉ በሙሉ በአህባሽ ሰዎች እንዲያዝ የተደረገ) በጋራ በሚዘጋጁ በሕገ መንግሥት ሥልጠናዎች ስም በሚሰጡ የአህባሽ ትምህርት ሰበካዎች ላይ ወሀቢያን እናወድማለን በሚል ሰበብ የየመስጊድ ኢማሞችን የመሰየም/የመሻር፣ የሚሰጡ እስላማዊ ትምህርቶችን ከአንድ ምንጭ (የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት) ብቻ እንዲተላለፍ፣ የጁምዓ ሰላት ኩጥባዎች (መልዕክቶች) በተመሳሳይ መልኩ ወጥ በሆነ ሁኔታ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ በሚተላለፉ መሠረት ብቻ እንዲሆን በይፋ እየተነገረ ነው፡፡ የአህባሽ ድርጅታዊ መዋቅር ከላይ እስከ ቀበሌ እንዲዘረጋ ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡

ይህ አካሄድ የአህባሽን የእምነት ሴክት የማይቀበሉ ኢማሞችንና ሙዓዚኖችን (የሰላት ጥሪ የሚያደርጉ) ለማስወገድ፣ ዓሊሞችን (በእስልምና የጎላ ዕውቀት ያላቸውን) ለማግለል ነው፡፡ በመጨረሻም ተወደደ ተጠላ የአህባሽ የእምነት ሴክት ብቻ በአገራችን እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ በሐረር ላይ በተደረገው (ሰኔ/ሐምሌ 2003) የመጀመርያው የአህባሽ ስብስባ/ሥልጠና የወጣውን የአቋም መግለጫ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ማየት ይቻላል፡፡

ከላይ የተመለከተው አካሄድ ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን የረሳ ይመስላል፡፡ አንደኛው በአገራችን በሰላማዊ ሁኔታ እምነቱ የሚያዛቸውን ብቻ እየፈጸሙ ከሌሎች ጋር በመግባባት የሚኖሩ ሌሎች የእስልምና ሴክት ተከታዮችን ሁሉ (ለምሳሌ በማስተማር ላይ ትኩረት የሚያደርጉትን የተብሊግ ጀመዓዎችንና ሌሎች አህለል ሱና ኡማዎችን ወይም የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጭራሽ እንደሌሉ ወይም መኖር እንደሌለባቸው በመቁጠር ሲሆን፣ ሌላው በአገራችን ያሉት አብዛኛዎቹ መስጊዶችና መድረሳዎች በሕዝቡ የተሠሩ መሆኑን ከግንዛቤ ያስገባ ነው (በጠቅላይ ምክር ቤቱ እገዛ የተሠሩ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው)፡፡ እዚህ ላይ የሕዝቡ ጥያቄ እነኝህ የአህባሽ የእምነት ሴክት አራማጆች እኛ በሠራናቸው መስጂዶችና መድረሳዎች ላይ አያገባቸውም፡፡ ሲፈልጉ እንደሌላው የእምነት ተከታዮች በራሳቸው የፀሎት ቤቶች ትምህርታቸውን ያስተምሩ፡፡ እኛ በሠራናቸው መስጂዶችና መድረሳዎች ሊያስገድዱ አይገባም የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ይህ ትክክለኛና ፍትሐዊ ጥያቄ ነው፡፡

ሌላው አህባሽ አንድ የእምነት ሴክት በመሆኑ የሚያራምደው እምነት (ዓቂዳ) አብዛኛው የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከሚከተለው ዓቂዳ ወጣ ያለ ስለሆነ እንኳን ማመን መስማትም የለብንም፡፡ እነሱም የራሳቸውን እኛም የራሳችንን ዓቂዳ እንከተል፤ በዚህ መንግሥት ሊተባበራቸው አይገባም፡፡ የሌላውን እምነት በሌሎች ላይ በግድ መጫን ሕገ መንግሥታዊ ስለሆነ የሚል አቋም የተያዘበት ነው፡፡

ለአንዋር መስጂድ ጥገናና የውኃ ፍጆታ ሒሳብ መክፈል አቅቶት የነበረው የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምንጩ ባልታወቀ በመቶ ሚሊዮኖች ብር በሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ መላ አገሪቱን ያካለለ ሥልጠናዎች መስጠቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሠልጣኞች ወደዱም ጠሉ በየደረጃው ሌሎችን እንዲያስተምሩ (Multipliers Effect) እያደረገ ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ጥያቄ በእስልምና ትምህርት አሰጣጥና ሌሎችን በግድ እንዲቀበሉ የማድረግ ሁኔታ ከመንግሥት ድጋፍ ማግኘት የለበትም ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል ያሰኛልና፡፡

የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ጥያቄ ትናንትናና ዛሬም በሰላማዊ ሁኔታ እየቀረበ ይገኛል፡፡ በቀጣዩም ሕገ መንግሥቱን መሠረት ባደረገ በሰላማዊ ሁኔታ በተመሳሳይ መልክ የሚቀርብ ይሆናል፡፡

ለአብነት ያህል ባለፉት በርካታ ሳምንታት በየጁምዓ ሰላት ወቅት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሙስሊሞች በአወሊያ ተገኝተው በሰላማዊ ሁኔታ ሰግደው፣ ዱዓ አድርገው፣ ተወያይተውና የጋራ ግንዛቤና አቋም ይዘው ሲለያዩ ነበር፡፡ አንዳችም ችግር አልተከሰተም፤ ሌሎች ችግር ፈጣሪዎች ሰዎቻቸውን አስርገው እንዳያስገቡ ከፍተኛ የፍተሻ ሥራ ሲሠራ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ ሰላም ፈላጊነት ማለት ምን ማለት ነው? መንግሥት በሚያወጣቸው መግለጫዎችጥቂት ግለሰቦችብሎ የሚገልጸው አብዛኛውን የሙስሊም ኅብረተሰብ ነውን? በመላ አገሪቱ በጥቃቅን ልዩነቶች መለስተኛ ሴክቶችን ፈጥረው የነበሩ የእምነቱ ተከታዮች በፀረ አህባሽ አቋም አንድ መሆናቸው ለእስልምና መስፋፋት ጥሩ አመለካከት ለሌላቸው ግለሰቦችና ተቋማት ራስ ምታት ቢሆንም፣ አብዛኛውን ሙስሊም ኅብረተሰብ ከትክክለኛ እምነቱ ለማስወገድ እየተደረገ ያለው የተቀነባበረ ጫና፣ የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ሰላማዊና ፍትሐዊ የሆነ እልህ አስጨራሽ ትግል እንደሚጠይቅ ሊታወቅ ይገባል፡፡

በመሆኑም ሕዝቡ በመንግሥት ሙሉ ትብብርና ድጋፍ እየተሰጠ የሚገኘው የአህባሽ ሥልጠናና ከዚህ በመነሳት ሌሎችን የእምነቱን ሴክቶች በግድ የመጨፍለቅ እንዲሁም ሕዝቡ በግድ እንዲቀበል የማድረግ ጥረት ይቁምልን፡፡ እምነታችንን በሰላም እናራምድ የሚለው የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ጥያቄና መንግሥትአክራሪ፣ አሸባሪ፣ ለልማት እንቅፋት፣ ወዘተበማለት ሰላማዊውን ሕዝብ ግራ ለማጋባትና ለመምታት እየተደረገ ያለው ዝግጅትና ምላሽ አራምባና ቆቦ ናቸው፡፡ ለሕጋዊና ለትክክለኛ ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ መስጠት ሲገባ ያልተገባ ሥዕል በመሳል የሌሎች እምነት ተከታዮች ስጋት ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ ፍትሐዊ ብቻ ሳይሆን ሥነ ምግባራዊ ጭምር  ነው፡፡ አገርን በእኩል እመራለሁ ከሚል መንግሥት የማይጠበቅ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ሚያዝያ 28 ቀን 2004 በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣሕገ ወጥ ቅስቀሳ ላይ የተሰማሩ የውጭ ዜጎች ከአገር ተባረሩበሚል የቀረበው ዜና የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ጥያቄ ከውጭ ኃይሎች ጋር ለማያያዝ የተደረገ ጥረት ነው፡፡ እንደተባለው የውጭ አገር ዜጎች በሕገወጥ ቅስቀሳ ላይ ከተያዙ ለምን ለሕዝቡና ለፍትሕ አካላት አልቀረቡም? ወንጀል ሠርተዋልና፡፡ ወንጀል የሠራ ደግሞ በግድ ለሕግ መቅረብ ነበረበት፡፡ ሁለተኛ ሰዎቹ ከመካከለኛው ምሥራቅ እንደመጡ ሲገለጽ ለምን አገራቸው ሳይነገር ቀረ? የክልሎችን ሁኔታ እንኳ ለጊዜው ተወት ብናደርግ የመላው ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ጥያቄ መቅረብ ከጀመረበት ካለፉት በርካታ ሳምንታት ወዲህ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ መስጂዶችም ሆነ በአወሊያ አንዳችም የተከሰተ የፀጥታ ችግር የለም፡፡

የሌለን ችግር እንዳለ በማስመሰል የእምነቱን ተከታዮች መምታት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ውጤቱ ለአገሪቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ ሕዝብና መንግሥት ይራራቃሉና፡፡ ዋናው መንግሥት በሰከነ አዕምሮና በገለልተኝነት ስሜት ሁኔታዎችን ቃኝቶ ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል፡፡

የመንግሥትም ሆኑ የግል ሚዲያዎች የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ጥያቄዎች ትክክለኛነት ማረጋገጥ ብሎም ለሕዝቡ ይፋ ማድረግ፣ የተሳሳቱ አዝማሚያዎች ካሉ ኅብረተሰቡን የማስተማር ብሎም የተሟላ መረጃ (Balanced Information) ለኅብረተሰቡ ማቅረብ የሙያ ግዴታቸው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ግንቦት 2 ቀን 2004 .. በወጣው እትሙየድብቁን ግብ ሴራ እናፍርሰውበሚል ርዕሰ አንቀጽ ያቀረበው እንደ አንድ የመረጃ ምንጭ የቀረበ ሳይሆን፣ እንደ መንግሥት ሆኖ (አንዳንችም ጥናት ሳያደርግ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ መድረሱ) ትዕዛዝ ማስተላለፉና የሕዝቡን ትግል ወዳልሆነ አቅጣጫ መፈረጁ የሚያሳፍረው ነው፡፡ ቢሆን እንኳ የራሱን ሳይሆን የመንግሥትን ትዕዛዝ ማስተላለፍ ሲኖርበት አልያም የችግሩን ትክክለኛ መንስዔ በምርመራ ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) ሊደርስበት ሲገባ፣ የሌለ መልዕክት ማስተላለፉ የሙስሊሙን ኅብረተሰብ በእጅግ እንደሚያስከፋ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ በመጀመርያ ሁሉም የእምነቱን ሴክቶች ያካተተ (አህባሽን ጭምር) ዓሊሞችና ምሁራን የሚሳተፉበት አገራዊ የውይይት መድረክ ቢዘጋጅ፣ የውይይቱ ውጤት ለሕዝቡ በተሟላ መልኩ ቢቀርብ፣ ቀጥሎም ሁሉም ሚዲያዎች፣ የሌሎች የእምነት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ተወካዮችና መንግሥት የጋራ መድረክ ፈጥረው ለቀረበው የመብትና የፍትሕ ጥያቄ በጋራ አገራዊ መፍትሔ እንዲሰጡ ቢደረግ ይበልጥ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

ሰላምና ብልፅግና ለአገራችን

No comments:

Post a Comment