Thursday, May 24, 2012

“ፊርደውስ” ዐይኔን አበራችልኝ!!


ካለፈው የሀምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ “ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በፅንፈኝነት የተመላውን የወሀቢያ እሳቤ ትተው በሊባኖስ ሰራሹ የአህባሽ ርእዮት መጠመቅ አለባቸው” የሚል ቅዠት መቃዠት የጀመረው “ልማታዊ መንግስታችን” ይህንን መንገድ እንዲተው ብንለምነው “ስም አጉዳፊዎች ናችሁ” እያለ ሲያላግጥብን ከረመ፡፡ መብትና ነጻነት መጠየቃችንን እንደ ወንጀል በመቁጠር “አገር ለመበጥበጥ የተነሱ የጥፋት ሀይሎች” የሚል ስም አውጥቶልን በሞኖፖል በያዘው የህዝብ ሚዲያ ሲሰድበን ቆየ፡፡ የአወሊያ ተማሪዎቻችን ያቀጣጠሉት ሰላማዊ የትግል ፋና መብራት ሆኖልን ለአራት ወራት ተቃውሞአችንን በሰላማዊ መንገድ በአደባባይ ብናሳይ “ዋ! ቀዩን መስመር እያለፋችሁ ነው! በዚህ ከቀጠላችሁ ትእግስቴ ያልቅና ባሻሁት መንገድ እደፈጥጣችኋለሁ” እያለ አስፈራራን፡፡ በአሳሳ ከተማ ንጹሃን ወገኖቻችን የጥይት እራት ካደረገ በኋላ “የተገደሉት ጂሀድ ሲቀሰቅሱ የተገኙ ጥቂት አሸባሪዎች ነው” በማለት ቀለደብን፡፡
የትላንትናው (May 23/2012) ግን ይገርማል!! ሚኒስትር ተብዬው ሺፈራው በሪፖርተር ጋዜጣ የለመደውን የስድብ ጋጋታ በህዝብ ፊት ሲደግመው ነገሩ ያላስቻላት ወጣት ፊርደውስ “ይህ ስድብ አሁንስ በዛ! ስድቡን አቁመህ በአስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ብንነጋር ይሻላል” ብትለው ደህንነቶች በኤሌክትሪክ ሾክ ገደሏት!! በጭካኔ አለንጋ ቀነጠሷት!!
አጂብ!! ሺፈራውም ሆኑ “ልማታዊው መንግስታችን” አመቱን በሙሉ ድራማ ሊሰሩብን ቢሞክሩም ከኪራሳ በስተቀር አንዲት ስሙኒ ትርፍ ማስመዝገብ አልቻሉም፡፡ አንዴ “ወሀቢያ” አንዴ “ሰለፊያ” እያሉ በቃላት ጨዋታ ሊያምታቱ ቢሞክሩም ከጥቂት ሆዳሞች ውጪ የተከተላቸው ሰው የለም፡፡ ድሮ “ሱፊያ” እና “ወሃቢያ” በሚል የለመዱትን ክፍፍል ትተው ከሰሞኑ “ነባሩ እስልምና” እና “አዲሱ እስልምና” የሚል ፈሊጥ ቢያመጡም የራሳቸውን አባላት እንኳ መሸወድ አልቻሉበትም፡፡ “በፊርደውስ ላይ የተወሰደው እርምጃ ግን የተስፋ መቁረጥ ምልክት ይመስላል፡፡
ዘይገርም ነገር!! ዓለም በሙሉ በሴቶች ላይ የሚወሰዱ የሀይል ጥቃቶችን ለማስቆም በሚጯጯኽበት በዚህ ዘመን አንድ መንግሰታዊ ተቋም አንዲት ሴት ወጣትን በኤሌክትሪክ ሾክ ጠብሶ ማስገደሉ ምን የሚሉት ጭካኔ ነው? ክቡሩን የሰው ልጅ ያለምንም ወንጀል እየገደለ መንግስታዊ ሃላፊነትን የሚመራ ህሊና ሊኖር ይችላል? ደግሞስ ፊርደውስን በኤሌክትሪክ ንዝረት ስለገደሉ ብቻ መብቱን ለማስከበር ይህንን ያሀል ርቀት የተጓዘውን ህዝብ ወደ ኋላ መመለስ ይቻል ይኾን?
የፊርደውስ ስቃይ ወንበሩን ብቻ ለማስጠበቅ ለሚታትረው “ጀግናው” ሚኒስትር ሽፈራውና ለደህንነቶቹ ጊዜያዊ ደስታ ፈጥሮላቸው ይሆናል፡፡ እኛ ሙስሊሞች ግን ይህንን መራራ ግፍ ለላቀ ጀብዱ  የሚያነሳሳ የትግል ጥሪ አድርገን ተቀብለነዋል፡፡ ለኛ መብትና ነጻነት የመጨረሻውን ዋጋ በመክፈል ሰማእት የሆነችው “ፊርደውስ” የብርታትና የቆራጥነት ምልክት ሆናልናለች፡፡ እኛም እርሷ ከሞተችበት መንገድ አናፈነግጥም፡፡ የ“ሺፌውን” የኤሌክትሪክ ወንበር ፈርተን እርሷ የሞተችለትን ዓላማ ከግብ ሳናደርስ አንቆምም፡፡ ፊርደውስን ብንከዳ የነገ ሰው አይበለን!
“ፈሪደውስ” መጨረሻዋ እንደስሟ ያማረ ሆኖላታል፡፡ ለ“ሸሂዶች” (ሰማእታት) ትልቅ ድግስ ያዘጋጀው አላህ በከፍተኛ ማዕረግ እንደሚቀበላት አንጠራጠርም፡፡
“ያ አላህ ከፊርደውስ ጋር በፊርደውስ አገናኘን!” አሚን!!!

1 comment:

  1. great job ubah and other brother may Allaah accept ur struggle

    ReplyDelete